የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ህክምና ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምእራፍ ተመረቀ

118

ሚያዚያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ህክምና ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ የልብ ህክምና መስጠት ዓላማ ያደረገ ማዕከል የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ቤከር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተገኙበት በዛሬው እለት ተመርቋል፡፡

ዶክተር ሊያ ታደሰ በፕሮጀክት ምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ እንደ አገር የልብ ህክምና የሚሰጡ ተቋማት ውስን ናቸው፤ የልብ ቀዶ ህክምና የሚሰጡ ተቋማት ደግሞ የሉም ማለት ይቻላል፡፡

በዚህም ምክንያት ታክመው መዳን እየቻሉ ህክምናው አገር ውስጥ ባለመኖሩ ብቻ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ወደ ውጭ ሔደው የሚታከሙ ቢኖሩም ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪና ለእንግልት እንደሚዳረጉም ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር በመረዳት መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ አሁን ላይ ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ህክምና  ማዕከል ማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ይፋ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚህ የመጀመሪያው ምዕራፍ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዩሮ ወጪ የተደረገባቸው የህክምና ግብዓቶች መሟላታቸውን አንስተዋል፡፡

ሁለተኛው ምእራፍ የህንፃ ግንባታ ሥራ መሆኑን ጠቁመው ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ምዕራፎች ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገባ በልብ ህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን ከመታደግ ባለፈ ለህክምና ወደ ውጭ አገር የሚደረገውን ጉዞ ያስቀራል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ቤከር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች አገራቸው የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

“አባቴ በልብ ህመም ነው ህይወቱን ያጣው፤ ስለዚህ የበሽታውን አደገኛነት አውቀዋለሁ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የልብ ህክምና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለመደገፍ በሚሰራው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እሰራለሁ” ብለዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ህክምና ማዕከል ፕሮጀክት ኃላፊ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል ለማስፋፋት ወደ 40 ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት በጀት ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ይህን ወጪ የኔዘርላንድ መንግሥት 50 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የልብ ህክምና መስጫ ማዕከላት ግንባታ ፕሮጀክት ለመቅረጽ መነሻ የነበረው የታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በምሥራቅ አፍሪካ የታወቀ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ህክምና መስጫ ተቋም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው፡፡