የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ቅድሚያ ይፈልጋል

580

ሚያዚያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመንግሥት ተቋማት የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት የአመራር ቁርጠኝነትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ምሁራን መከሩ።

የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ አለመሆን፤ ጠንካራና ተሻጋሪ የሆነ ተቋማዊ ስርአት የመገንባት ችግር ውጤት መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ምሁራን ገልጸዋል።

በአካዳሚው የአመራር አሰልጣኝና አማካሪ ዶክተር እሸቴ አበበ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቋቋሙበት ዋነኛ ምክንያት ዜጎችን ለማገልገልና ጥያቄያቸውን ለመመለስ መሆኑን አንስተዋል።

ነገር ግን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተቋማዊ  የአሰራር ሥርዓትን ባህል በማድረግ በኩል በአመራሩ ዘንድ የቁርጠኝነት ችግር እንደሚስተዋል በመልካም አስተዳደር ላይ የተደረጉ ጥናቶች  እንዳመላከቱ ጠቁመዋል።

ተቋማቱ ከባህሪያቸው አንጻር የራሳቸውን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ የስነ-ምግባር መርሆች በመቅረጽ የሚመሰረቱ ቢሆንም ወደ ተግባር ሲገባ ግን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በስፋት እንደሚስተዋልም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም አመራሩ ተቋማዊ ግንባታ ላይ ትኩረት በመስጠት አገርና ህዝብን ለመለወጥ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

አመራሩ ለችግሩ መፍትሔ አመላካች ሐሳቦችን በማፍለቅ፣ ሠራተኛውን በማሳተፍና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘላቂ ሥርዓት መዘርጋት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ በአመራሩ ላይ የሚስተዋሉ የመሪነት ሚና አለመወጣትና ሌሎች ክፍተቶችን በመለየት አገራዊ የአመራር ፖሊሲ እያረቀቀ መሆኑን ዶክተር እሸቴ አበበ ጠቁመዋል።

የአመራርና ፖሊሲ ጉዳዮች ተመራማሪ ጥላሁን ወርቁ በበኩላቸው፤ አብዛኛው የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግልጽ የአሰራር ሥርዓት አለመዘርጋታቸው ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እንዳይሰጡ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

እየጨመረ ከመጣው አገልግሎት ፈላጊ ጋር ሊጣጣም የሚችል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ጠንካራ ተቋማት የአሰራር ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተቋማት ግንባታ ውስጥ አሰራር፣ የሰው ኃይልና መዋቅር ወሳኝ መሆናቸውን በመዘርዘር የተቋማት መሪዎች ቢቀያየሩ እንኳን ዘላቂ የአሰራር ሥርዓት ከተዘረጋ በአገልግሎቱ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖር አስረድተዋል።

ተቋማት በየዓመቱ ያሉበትን የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ለሚለኩ ተቋማት ክፍት መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት አለመኖር ለሙስና ተጋላጭ ስለሚያደርግ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ግልጽ አሰራር መተግበር ወሳኝ መሆኑን ምሁራኑ አንስተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም