ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

94

አዳማ ሚያዝያ 17/2014 (ኢዜአ) ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር አንድነትና ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የአዳማ ከተማና አካባቢዋ የሀገር ሽማግሌዎችና ሀደ ሲንቄዎች።

ለኢዜአ ሀገራዊ ምክክሩን በተመለከተ በአዳማ ከሀገር ሽማግሌዎችና ሀደ ሲንቄዎችጋር ቆይታ አድርጓል ።

አስተያየታቸውን ከሰጡ መካከል የአገር  ሽማግሌ  አቶ ፈይሳ  መገርሳ  እንደገለጹት  ቁጭ ብሎ መመካከር ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን ከማረጋገጥ ባለፈ ተስማምተን በጋራ ለመኖርም ወሳኝ ሚና አለው።

“በምክክር የተግባባንበት ጉዳይ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሲደረግ ነው በሰላም መኖር የሚቻለው” ያሉት አቶ መገርሳ፤ በሀገራዊ ምክክሩ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ዑጋዞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ጉዳይ የሚመለከተው ሁሉ በመሳተፍ  ለስኬታማነቱ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

“የውጭ ሃይሎች ሀብታችን ጭምር እንዳንጠቀም ጭምር እየፈጠሩብን ያለው ጫና የውስጥ ጥንካሬያችንን ክፍተት በማየት ነው” ያሉት አቶ መገርሳ፤ መመካከሩ ውስጣዊ አንድነታችንን እንድናጠናክር ያስችለናል” ሲሉ አክለዋል ።

“ኢትዮጵያውያን ተዋልደን ተጋብተን በአንድነት የኖርን ህዝቦች ነን ፤ችግራችንን ቁጭ ብለን በመምከር መፍታትና የለማች አገር መፍጠር ይኖርብናል” ሲሉም አመልክተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ መካሄድ ከነበረበት ጊዜ የዘገየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቱለማ ኦሮሞ ሃደ ሲንቄ አፀዱ ቶላ ናቸው።

“ለሀገራችን እርቀ ሰላም ለማውረድና አንድነትን ለማጠናከር የሚያዋጣንና የሚያስኬደን መንገድ መመካከር ነው” የሚሉት  ሃደ ሲንቄ፤ “ሃደ ሲንቄዎች የኦሮሞ ብቻ ሳንሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር እናት በመሆናችን በሀገራዊ ምክክሩ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን” ብለዋል።

“ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ምክክሩ ይመለከተኛል ብለው መሳታፍ  አለበት፤ ምክክሩም ተንጠልጥሎ መቅረት የለበትም ፤  እስከ  ከቀበሌ ወርዶ ህዝቡ ሊሳተፍበት ይገባል “ብለዋል።

የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች የእርቅና የሰላም ጥምረት ሊቀ መንበር ሃጂ ሁሴን ሃሞ በበኩላቸው  ሀገራዊ ምክክርና እርቅ ማካሄድ በየቦታው  ያለውን  ግጭት፣  የንብረት  መውደምና የህይወት መጥፋት በዘላቂነት ለማስቀረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባትና  ግጭቶችን  ለማስወገድ  ፋይዳው  የጎላ በመሆኑ  ህብረተሰቡን  ግንዛቤ  በማስጨበጥ  ንቁ ተሳትፎ   እንዲኖረው  ማድረግ  እንደሚገባ   ሃጂ ሁሴን አመልክተዋል ።