በዞኑ ለመኸር እርሻ ከ3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጀ

187

አዳማ ሚያዝያ 17/2014 /ኢዜአ/ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በመኸር እርሻ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ከ3 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስተዋቀ።

የህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለፁት ለ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን ከ439 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ  ነው።

በምርት ዘመኑ ስንዴ፣ የጤፍ፣ ጥራ ጥሬና የሌሎች ሰብሎች ምርታማነት በሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ሳቢያ እንዳይቀንስ 4 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ መዳበሪያ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በዞኑ 10 ወረዳዎች በተቀናጀ የአርሶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ርብርብ እስካሁን ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱ ተናግረዋል።

ለመኸር እርሻ ከ594 ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈል ጠቁመው እስካሁን ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ በዩኒዬኖች በኩል ለመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት መድረሱን ገልጸዋል።

ከባዮ ጋስ ተረፈ ምርቶችና የመደበኛ ኮምፖስት ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን  አቶ መስፍን  ገልጸው፤ የግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የቦራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ደሜ ቆርቾ እንደገለጹት በወረዳው ከ380 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየተዘጋጀ ነው።

የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ንረትና የአቅርቦት እጥረት ችግርን ለማቃለል አርሶ አደሩ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ማካካስ እንዲችል የንቅናቄ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም ከ100 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰው እቅዱን ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ጣቢያው ባለሙያ አቶ ፀጋ ሸንቁጤ እንዳሉት በሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር ምክንያት በመኽር እርሻ ላይ እጥረት እንዳይገጥም ኮምፖስት እየተዘጋጀ ነው።

በተለይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአጭር ጊዜ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ የማራቢያ ትሎች ከጉደር አምጥተው በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት  የአፈር ለምነቱን የሚጠብቅ መሆኑን አመልክተዋል።

አርሶ አደር መሰረት ቸኮል በበኩላቸው በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ከባዮ ጋዝ ተረፈ ምርትና መደበኛ ኮምፖስት እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልጸው፤ ለሰብል፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።