የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተመረቀ

236

ሚያዚያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት ተመረቀ።

በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለውና አስተማማኝ የልብ ሕክምና አገልግሎት መስጠትን ዓላማው ያደረገው ፕሮጀክቱ በኔዘርላንድስ መንግስት ድጋፍ የተጀመረ መሆኑ ተገልጿል።

ከ39 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በጀት የተያዘለት የልብ ሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታው 50 በመቶ ወጪው በኔዘርላንድስ መንግስት ይሸፈናል የተባለ ሲሆን ቀሪው 50 በመቶ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

ማዕከሉ የልብ ሕክምና አገልገሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ያለውና በዘርፉ የተለያዩ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።

የልብ ሕክምና ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶች የተሟሉለት ባለ 97 አልጋ ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል።

የማዕከሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ ሲመረቅ በአፍሪካ ብቸኛ የሆነ ልብ ሳይከፈት ሕክምና ማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ ማሽንም ተገዝቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም