በመዲናዋ የትንሳኤ በዓል ምንም አይነት አደጋ ሳያጋጥም ተከብሮ ውሏል

250


ሚያዝያ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመዲናዋ በበዓል ዋዜማ በአንድ ጋራዥ ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ቢደርስም የትንሳኤ በዓል ምንም አይነት አደጋ ሳያጋጥም ተከብሮ መዋሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡


የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ፤ የትንሳኤ ዋዜማ ምሽት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ግምቱ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል።


የእሳት አደጋው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በአንድ ጋራዥ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፤ የንብረት ውድመት ከማስከተሉ በስተቀር በሰው ላይ ጉዳት አለማድረሱን ገልጸዋል።


አደጋውን ለመቆጣጠር ሰባት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች እና 47 የህይወት አድን ሰራተኞች ተሰማርተው ባደረጉት ፈጣን ምላሽ እሳቱ ሳይዛመትና የባሰ ጉዳት ሳያደርስ ማጥፋት መቻሉን ተናግረዋል።


አደጋውን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት ማዳን መቻሉንም ጠቁመዋል።


በአዲስ አበባ በዋዜማው ከተከሰተው አንድ የእሳት አደጋ በስተቀር በትንሳኤ በዓል ምንም አይነት አደጋ ሳይደረስ በሰላም መጠናቀቁን አቶ ንጋቱ ገልጸዋል።


በበዓሉ አከባበር ወቅት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መንስኤዎችን በቅጡ በመረዳት ማህበረሰቡ ያደረገው ጥንቃቄ ለበዓሉ ሰላማዊነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።


ከሚሽኑም የአደጋ መንስኤዎችን ህዝቡ እንዲረዳና ጥንቃቄ እንዲያደረግ ቀደም ብሎ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ማከናወኑ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።


በመሆኑም የማህበረሰቡ ጥንቃቄ ቀጣይነት እንዲኖረውና አደጋን የመቀነስ ሥራ የጋራ ኃላፊነት አድርጎ መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


መጪው የኢድ በዓል ሲከበርም ተመሳሳይ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም