በአዳማ ከ2ሺህ 900 በላይ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ ደረጃ ለሚኖሩ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ

179

ሚያዝያ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ ከ2ሺህ 900 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የትንሣዔ በዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የተደረገው የከተማው አስተዳደር ባለሃብቶችን በማስተባበር ባሰባሰበው ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ እንደሆነ ተገልጿል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በወቅቱ እንዳሉት፤ ድጋፉ ሁሉም ካለው በማካፈል ምንም ገቢ የሌላቸውና መግዛት የማይችሉ አቅመ ደካሞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ነው።

በተለይ በዚህ በአስቸጋሪ ወቅት በመተጋገዝ ያለንን ተካፍለን ማዕድ በማጋራት የትንሣዔንና ኢድ አል ፈጥር በዓላት ማሳለፍ አለብን ብለዋል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም በከተማዋ 18 ቀበሌዎች ለሚኖሩ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ የዳቦ ዱቄት፣ሩዝ፣ የምግብ ዘይት፣ዶሮ፣ በጎችና ፍየሎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ጠጅቱ ቶላ በሰጡት አስተያየት፤ ለበዓል መዋያ የሚሆኑ በግ ፤የዳቦ ዱቄትና ዘይት አግኝተናል በጣም ነው ደስ ያለን” ብለዋል።

ለዚህም የከተማ አስተዳድሩን አመስግነዋል ።ወይዘሮ ሀቢባ ዘምዘም በበኩላቸው ”እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ፤ ምንም ተንቀሳቃሼ መስራት አልችልም፤ አስተዳድሩ ቀደም ሲል የመኖሪያ ቤት አበርክቶልኛል” ብለዋል።

በተጨማሪም የበዓል መዋያ የዳቦ ዱቄትና ፍየል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

”አቅመ ደካማ ነኝ፤ ለዕለት ጉርስ ከቤተሰቦቼ ጋር እየተቸገርኩ ነበር፤ አሁን አስተዳድሩ አስታውሶን ዓመት በዓሉን ካላቸው እኩል ተደስተን እንድናሳልፍ አድርጎናል፤ እናመሰግናለን” ያሉት ደግሞ አቶ ተገኔ ካሳ ናቸው።