የትንሳኤ በዓልን ስናከብር የተቸገሩትን በማጋራት ሊሆን ይግባል----- የሃይማኖት አባቶች

167

ደሴ/ ደብረ ብርሃን  ሚያዚያ 15፤ 2014 ዓም /ኢዜአ/ ''የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ምዕምናኑ የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ፣ በመርዳትና በአብሮነት ሊሆን ይገባል'' ሲሉ የደቡብ ወሎና የሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳሳት አስገነዘቡ።

የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጻጻስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አትናቴዎስ የትንሳኤ በአልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ ሁሉም በየእምነቱ መፀለይና ማገዝ አለበት።

ምዕምናኑም የትንሳኤን በዓል ሲያከብር የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ያለውን ተካፍሎ በአጋርነት ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሁሉም ያለ ብሔርና እምነት ልዩነት ተከባብሮ፣ተጋግዞና ተረዳድቶ በጋራ በዓሉን እንዲያሳልፍ መክረዋል።

"የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ከአንድነት ውጭ አማራጭ የለንም" ያሉት አቡነ አትናቴዎስ "ሁሉም በየእምነቱ ስለ ሰላምና ስለ አንድነት ማስተማር ይጠበቅበታል"ብለዋል።

እርሳቸውም በዓሉን ከ600 ከሚበልጡ አቅመ ደካሞች ጋር ለማሳለፍና ለማስገደፍ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ውሎ ዞን ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ መምህራን ብርሃነ ህይወት እውነቱ በበኩላቸው "በዓሉን ከተፈናቃይ፣ አቅመ ደካሞችና ችግረኞች ጋር ማሳለፍ ይገባል" ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ዛሬ በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም በመገኘት አቡነ አትናቴዎስን የጠየቁ ሲሆን ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

''በተመሳሳይ የትንሳኤን በዓልን ስናከብር በፀጥታ መታወክና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በመርዳት ሊሆን ይገባል'' ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምጦስ ናቸው።

"ትናንት ቤት ንብረት የነበራቸው ዛሬ ላይ ደግሞ በፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ሆነው በዓሉን ሲያከብሩ ከጎናቸው በመሆን ማጽናናት ይገባል" ሲሉ ገልፀዋል።

የሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ 185 አቅመ ደካማ ወገኖች ለትንሳኤ በዓል መዋያ ለእያንዳንዳቸው 500 ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለአበሻ አረጋዊያን ማህበር 15 ሺህ ብርና በሸዋ ሮቢት ከተማ ለሚገኙ ችግረኛ ቤተሰቦች 283 ሺህ ብር ግምት ያለው 40 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የትንሳኤ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተባበር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም