በወላይታ ሶዶ በሞተር ሳይክል ስርቆት የተጠረጡ አራት ግለሰቦች ተያዙ

125

ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዚያ 15/2014 (ኢዜአ) በወላይታ ሶዶ ከተማ የሞተር ሳይክል ስርቆት ወንጀል በማስፈጸምና በመፈጸም ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ አራት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥ ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ዋና አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ሞተር ሳይክል በመስረቅና በማሰረቅ ወንጄል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ተይዘዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በወላይታ ሶዶ ከተማ ድል በገሬራ ቀበሌ ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ ተከራይተው በተቀመጡበት በግለሰብ መኖሪያ ቤት ከአንድ ሞተር ሳይክል ጋር እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

እጅ ከፍንጅ የተያዘው ሞተር ሳይክል ትላንት በሞተር ሳይክል አከራይነት ከተሰማራ ግለሰብ የተዘረፈ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰዋል ።

ግለሰቦቹ የተለያየ ዘዴ በመጠቀም የሞተር ስርቆት እንደሚፈጽሙ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ክትትል ሲደረግባቸው የቆዩ መሆናቸውን ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አስታውቀዋል ።

በተለይ በግለሰብ ግቢ በመግባትና ዜጎች ለግል ስራ ሲሰማሩ ሞተር ሳይክል በሚያቆሙበት ቦታ አሳቻ ሰዓት እየጠበቁ በተመሳሳይ ቁልፍና በተለያየ ዘዴ ሞተሮችን በማስነሳት በመስረቅና በማሰረቅ ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ተጠርጣዎች መሆናቸውን አብራርተዋል ።

የሞተር ሳይክል ኪራይ አገልግሎት በመስጠት ህይወታቸውን የሚመሩን በማስፈራራትና በመንጠቅ ጭምር የሞተር ሳይክሎችን ወደ አጎራባች ዞኖች እንደሚያሻግሩና ከአጎራባች ዞኖችም ተባባሪ በማፍራት ተመሳሳይ ወንጀል የሚፈጽሙ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

ግለሰቦቹ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ አስታውቀዋል ።

በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የሚከበረው የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት በማድግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አክለዋል ።

በተለይም የተለያየ ዘዴ በመጠቀም የስርቆት ወንጄል ለመፈጸም የበዓል ወቅት ግርግር አመቺ መሆኑን አንስተው ህብረተሰቡ የወንጀሉ ሰለባ ላለመሆን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ  ዘውዴ አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም