በሆሳዕና የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለዘማችና ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ድጋፍ ተደረገ

164

ሆሳዕና ሚያዝያ 14/2014 (ኢዜአ )... የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ለዘማች ቤተሰቦችና ለአቅመ ደካሞች ለትንሳኤ በዓል መዋያ የሚሆን ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስና ገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቲርካሶ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው ለ187 የዘማች ቤተሰቦችና ለአቅመ ደካሞች ነው።

ድጋፉ ሩዝ፣ ማኮሮኒ፣ ዘይት፣ አልባሳት ጨምሮ ሌሎች ለበዓል መዋያ የሚሆኑ የፍጆታ ምርቶችንና ጥሬ ገንዘብን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱ ድጋፉን በህልዉና ዘመቻ የተሳተፉ የዘማች ቤተሰቦችንና አቅመ ደካሞች ያደረገው ከተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍሎች በማሰባሰብ ነው ብለዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ካለው ለሌሎች በማካፈልና ለመልካም ነገር ልቦናውን በማነጽ እንዲያከብርም አሳስበዋል።

በከተማው አራዳ ቀበሌ ድጋፍ ከተደረገላቸው የዘማች ቤተሰቦች መካከል ወይዘሮ ጥሩነሽ ግርማ ባለቤታቸው በህልውና ዘመቻው መሰዋታቸውን ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

ስምንት ኪሎ ግራም ሩዝና ማኮሮኒ፣ አልባሳትና 1ሺህ ብር ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰው፤ ባለቤታቸው ከጎናቸው ባይኖርም አስታዋሽ በማግኘታቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።

የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን ከልጆቻቸው ጋር ያለምንም ችግር ለማሳለፍ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ እታገኘሁ በቀለ በበኩላቸው የሚደግፋቸው ሰው ባለመኖሩ አራት ልጆቻቸውን ልብስ በማጠብ በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ከልጆቻቸው ጋር እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም