ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ከተፈናቀሉ ወገኖችን ጋር ማሳለፍ እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ

104

ሰቆጣ፣  ሚያዚያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የትንሳኤ በዓልን ስናከብር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ሊሆን ይገባል" ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዋግ ኽምራ ሊቀ ጳጳስና የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን የሰቆጣ አጥቢያ ምክትል ሰብሳቢ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዋግ ኽምራ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም በዓሉን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያና በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመደገፍ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ "ጊዜው የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘን፣ ስብዕናን የማረጋገጫ በመሆኑ የወገኖቻችንን ችግር በመጋራት ማክበር ይገባል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ያጋጠሙንን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች በጋራ በመደጋገፍና በመተዛዘን ልንቋቋመውና ልንሻገረው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር በማሰብ  ባለፉት ወራት ኢትዮጵያዊያን ላደረጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አቡነ በርናባስ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንገላዊያን ቤተክርስቲያን የሰቆጣ አጥቢያ ምክትል ሰብሳቢ አየለ አለባቸው በበኩላቸው በዓሉ የመረዳዳትና የመተሳሳብ ተምሳሌት በመሆኑ ምእመኑ የተቸገሩና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና አብሮ በማሳለፍ እንዲያከብር ጠይቀዋል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች ሲያደርግ የነበረው የመረዳዳት ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አቡነ በርናባስ የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን ጾም ለማስፈታት ባቀረቡት ጥሪ 32 ሰንጋዎችን ማዘጋጀት እንደተቻለ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም