በጋምቤላ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ ነው

125

ጋምቤላ ፤ ሚያዝያ 14/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የምግብ ዘይትና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች ገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኡቦንግ ለኢዜአ እንዳሉት፤  ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በምግብ ነክ ፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

በተለይም ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ  በህዝቡ የተነሱ ቅሬታዎች ለመፍታት የ90 ቀናት ዕቅድ ተነድፎ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቋሙ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ከተማና አካባቢ ከሁለት ሳምንት በፊት ተከስቶ የነበረው  የዘይትና የስኳር የፍጆታ ምርቶች እጥረት ችግር አሁን ላይ እየተቃለለ መረጋጋቱን ገልጸዋል።

በተለይም ወደ ክልሉ በገባው 100 ሺህ ሊትር የሚጠጋ የምግብ ዘይት  ውድ የነበረው ዋጋ ዝቅ በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት የተቻለበት አንዱ ማሳያ  መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ የምግብ ዘይትና ሌሎች ፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ የተሻለ ቢሆንም  በበግ፣ በፍየል፣ በቀንድ ከብትና በዶሮ ላይ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።

በዚህ ዘርፍ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት የእርድ እንስሳት ከሚመጣባቸው አካባቢዎች ያለው የዋጋ ሁኔታ እየተጠና ነው ብለዋል።   

በጋምቤላ ከተማ የእርድ እንስሳት ለመግዛት ሲዘዋወሩ  ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማች አቶ ሙላቱ ታደሰ  በሰጡት አስተያየት፤ አሁን ላይ ያለው የበግና የፍየል ዋጋ በገና በዓል ላይ ከነበረው በእጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በአምስት ሺህ ብር ይገዙት የነበረው በግና ፍየል ወደ 10 ሺህ ብር ቢደርስም በዓሉን እንዳቅማቸው ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከበግና ፍየል ነጋዴዎች መካከል አቶ አውራሪስ አየለ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የበግና ፍየል ዋጋ ቀደም ሲል ከነበረው ጨምሯል ብለዋል።

ከሚያመጡበት አካባቢ የአቅርቦት ችግር ሳያንስ፤ የዋጋ ጭማሪ እንደታየ ነው ያመለከቱት።

በሉካንዳ ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ተኬ ደፋ፤ ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በቀንድ ከብት ላይ እስከ 30 በመቶ የሚሆን የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።

ለገና በዓል 65 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረውን በሬ አሁን 80 ሺህ ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በጋምቤላ ከተማ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው ቀደም ሲል በኪሎ 40 ብር የነበረው ቀይ ሽንኩርት የ10 ብር ጭማሪ ሲያሳይ፤  ቅቤ እስከ  550 ብር ዋጋ እየተጠየቀ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም