መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀረበልን አትክልትና የምግብ ዘይት ተጠቃሚ አድርጎናል-የሐረር ነዋሪዎች

82

ሐረር ሚያዝያ 13/2014(ኢዜአ) መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ ባቀረበው የአትክልትና የምግብ ዘይት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በዓሉ አቅምን ባገናዘበ መልኩ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካክል ወይዘሮ አስቴር በቀለ እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ባመቻቸው የቅዳሜ ገበያ አንድ ኪሎ ግራም ሽንኩርት ገበያ ላይ ከሚሸጠው በተሻለ ዋጋ በ28 ብር ገዝተዋል።

በዓሉን አቅምን ባገናዘበ መልኩ እንደሚያሳልፉ ገልጸው፣ መንግሥት በተለይ እንደ ስኳር፣ የዳቦ ዱቄትና ሌሎች ሸቀጦችንም እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ ፍቃዱ ፀጋዬ እንዳሉት የክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች ፆም ላይ ገበያው መመቻቸቱ ገበያውን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በገበያው አትክልትና ሌሎች ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ መሆን እንዳስቻላቸውና ገበያውንም እንዳረጋጋው ተናግረዋል።

የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማገናዘብ ህዝቡ የተጋነነ ወጪ ከማውጣት በመታቀብ፣ አቅምን ባገናዘበ መልኩ በዓሉን ማሳለፍ እንዲያሳልፍም መክረዋል።

መንግስትንም ከማማረር ይልቅ እያበረከተልን የሚገኘውን አቅርቦት መደገፍ አለብንም ብለዋል።

ወይዘሮ አኒሳ ሁሴን በበኩላቸው የከተማው ነዋሪዎች የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጥን ከሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ  እያቀረበ ያለውን መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጥን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በከተማው የሚገኘው የመገናኛ ሸማቾች ሃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር የቁጥጥር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ያሬድ ማሞ "በመንግስት የሚቀርብልንን ዘይትና ሌሎች ሸቀጦችን ለሁሉም ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ የዋጋ ንረቱን የማረጋጋት ስራ እየሰራን እንገኛለን"ብለዋል።

በተለይ ከምግብ ዘይት አቅርቦት ጋር በተያያዘ አሁንም እጥረት ስለሚታይ መንግሥት መፍትሄ እንዲፈልግለት ጠይቀዋል።

የሐረሪ ክልል ንግድ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቡሽራ አልዩ እንዳሉት የትንሳኤ በዓልንና የረመዳን ፆምን በማሰብ  በአሁኑ ወቅት በከተማው የቅዳሜ ገበያ ሳምንቱን ሙሉ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

በገበያውም የአቅርቦት ችግሮችን ለማቃለል ኮሚቴ ተቋቁሞ በመሥራት ላይ እንደሚገኝና በተለይ 120ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት እየተከፋፈለ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም