ተዘዋዋሪ ችሎቱ በሰዎች የግድያ ወንጀል ከተከሰሱ 170 ሰዎች መካከል በአራቱ ላይ የቅጣት ወሳኔ አሳለፈ

231

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 13 /2014 (ኢዜአ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳ እና አካባቢው አንደኛ ተዘዋዋሪ ችሎት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ያሶ ወረዳ በተከሰተ ግጭት በሰዎች ግድያ በእነፈቀደ ጫብዴ የወንጀል ክስ መዝገብ ከተከሰሱ 170 ሰዎች መካከል አራቱ እስከ ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስታወቀ፡፡

ችሎቱ ቀሪ 13 ተከሳሾች የአቃቢ ህግ ምስክር ስላልቀረበባቸው በነጻ ሲሰናበቱ 153 ተከሳሾች ደግሞ በፖሊስ ተፈልገው ስላልተገኙ የወንጀል ክስ መዝገባቸውን ለጊዜው እንዲቋረጥ አዟል፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቢህግ ዘርፍ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸው፤  በክልሉ ካማሽ ዞን ያሶ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ከግንቦት 2010 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም. ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡

በግጭቱ የ46 ሰዎች ህይወት ሲልፍ፤በርካታ ሰዎች ከአካባቢው እንደተፈናቀሉና  ከ310 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመ የጠቅላይ አቃቢ ህግ ዘርፍ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ የመግደል ሙከራ መደረጉንም የጠቅላይ አቃቢህግ ዘርፍፉ ጠቅሷል፡፡

ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ አቃቢ ህግ በአጠቃላይ 170 ሰዎች ላይ የእርስ በእርስ ጦርነት ማስነሳት፣ በሰዎች ግድያ፣ከባድ ዝርፊያ ንብረት ማውደምን ጨምሮ በ59 የወንጀል ክስ መዝገቦች እንደመሰረተባቸው ዘርፉ አስታውቋል፡፡

ከ70 ገጽ በላይ በተዘረዘረው በዚሁ የወንጀል ክስ መዝገብ አቃቢ ህግ ከ100 በላይ የሰው፣  የሰነድ እና የህክምና ማስረጃዎችን ማቅረቡ ተብራርቷል፡፡

ከአጠቃላይ የወንጀሉ ተከሳሾች መካከል በማረሚያ ቤት ሆነው ክሱን ሲከታተሉ የቆዩት 17 ተከሳሾች እንደሆኑ የጠቅላይ አቃቢህግ ዘርፍ አመልክቷል፡፡

ከመካከላቸውም አራት ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ማስረጃ ሊከላከሉ ባለመቻላቸው ተዘዋዋሪ ችሎቱ ትናንት በአሶሳ ከተማ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህም  23ኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ኩምሳ መገርሳ ቦካ እና 55ኛ ተከሳሽ ሻምበል ዳኘው ሂናሃዱ እያንዳን ዳቸው በሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ዘርፉ አስታውቋል፡፡

እንዲሁም 19ኛ ተከሳሽ ተክሌ አቦሴ ሻዊ በሰባት ዓመት ፤ 13ኛ ተከሳሽ ኪዳኔ ዓለሙ በርሄ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተዘዋዋሪ ችሎቱ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል፡፡

በችሎቱ ቀርበው የወንጀል ክስ ሲከታተሉ የነበሩ ቀሪ 13 ተከሳሾች የአቃቢ ህግ ምስክር ስላልቀረበባቸው ከክሱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ተዘዋዋሪ ችሎቱ በነጻ እንዳሰናበታቸው ተመልክቷል፡፡

በዚሁ በእነፈቀደ ጫብዴ የክስ መዝገብ ስማቸው የተዘረዘሩ ሌሎች 153 ተከሳሾች ደግሞ በፖሊስ ተፈልገው ስላልተገኙ የቀረበባቸው የወንጀል ክስ መዝገቦች ለጊዜው እንዲቋረጡ ተዘዋዋሪ ችሎቱ ውሳኔ ማሳለፉን ዘርፉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም