መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለስኬቱ አዎንታዊ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል

82

ሚያዚያ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለምክክሩ ስኬት አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ አሳሰቡ።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኮሚሽኑ ተግባር፣ ኃላፊነትና ቀጣይ ስራዎች እንዲሁም በአገራዊ ምክክሩ የመገናኛ ብዙኃን ሚናን በሚመለከት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን  አመራሮች ጋር  ዛሬ ውይይት አካሂዷል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በወቅቱ መገናኛ ብዙሃን ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰብን የሚያስተሳስር ድልድይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የውይይት መድረኩም ይህን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንድትረጋጋ የማይፈልጉ አንዳንድ አካላት በኮሚሽኑ ላይ ሀሰተኛ ዘመቻ ሲያደርጉ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡

"አገራዊ ምክክሩ የአገር ፕሮጀክት ነው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙሃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ በኃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በዚህም መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክር ሂደትን ከሚያደናቅፉ ተግባራት በመቆጠብ ለምክክሩ ስኬት አዎንታዊ ሚና መጫወት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

መገናኛ ብዙሃን አገራዊ ጉዳዮች እንዲሳኩ መስራት እንደሚችሉ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ማሳየታቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ መረጃ የሚሰጥበትና የሚቀበልበት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ መገናኛ ብዙሃን የምክክር ሂደቱን የሚዘግቡበት የሥነምግባር ኮድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃን ለአገራዊ ምክክር ሀሳብ የቀረቡና ሥነ-ምግባር ያላቸውን ጋዜጠኞችን መመደብና ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም