በዞኑ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማትና ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

100

ደብረ ብርሀን እና ድሬዳዋ ሚያዚያ 12/ 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት እና ለተፈናቀሉ ወገኖች 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የሕክምና ቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ተደረገ።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችም የፋሲካ በዓልን እና የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ግምታቸው 4 ሚሊዮን የሆነ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ነው።

የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር መንግሥቱ አስናቀ ድጋፉን ሲያስረክቡ ድጋፉ የተደረገው የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት የወደሙና የተዘረፉ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ነው ብለዋል።

ድጋፉ የእናቶችና ህፃናትን ጤና አገልግሎት ለማጠናከር የሚግዙ የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች፣ የማዋለጃና የህክምና አልጋዎች፣ ማቀዝቀዝዎችና ለአነስተኛ ቀዶ ሕክምና መሳሪያዎችን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም 10 የጤና ባለሙያዎች በጦርነቱ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በስነልቦና እያከሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን በበኩላቸው ድርጅቱ ቀደም ሲልም ከመጀመሪያ የጤና መርሃ ግብር ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግላቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

የህክምና መሳሪያዎቹ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት እንደጉዳት መጠናቸው ለይቶ በፍትሃዊነት እንደሚከፋፈሉም አረጋግጠዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ "በተለይም በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት እስካሁን አገልግሎት መስጠት ላልጀመሩ የጤና ተቋማት ቅድሚያ ይሰጣል" ብለዋል።

በተመሳሳይ ትውልድን መታደግ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ከሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  የምግብ እህል ድጋፍ አድርጓል።

የደርጅቱ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ለማ ደገፉ እንደገለጹት እርስ በርስ መደጋገፍ የኢትዮጵያዊነት አኩሪ እሴት ነው።

ድርጅቱ አሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆች በአሰባሰበው ገንዘብ 105 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ በበኩላቸው በደብረ ብርሀን ከተማ 21 ሺህ ተፈናቃዮች እንዳሉ አስረድተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 17ሺህ የሚሆኑት በስድስት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙና የዕለት ጉርስ  ድጋፍ እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ ዜና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆች የፋሲካ በዓልና የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ በድሬዳዋ ለሚኖሩ 200 አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ለያንዳንዳቸው 1ሺህ ብር መደረጉ ተገልጿል።

የድሬዳዋ የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አቤል አሸብር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በማህበር ተደራጅተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ወዲህ የተበታተነውን ድጋፍ በቅንጀት ለማድረግ ተችሏል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ድጋፉን ሲረከቡ እንዳሉት፣ በውጭ ያሉ የድሬዳዋ ተወላጆች ለችግር የተጋለጡ 100 ህጻናትን በቋሚነት እየደገፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተወላጆቹ ያደረጉት ድጋፍ እርስ በርስ መረዳዳትን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸው፣ ለድሬዳዋ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት የተጀመረው ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም