ድርጅቱ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለውን ቦታ ተረከበ

154

ሚያዚያ 12 /2014 (ኢዜአ)  የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት የኩላሊት እጥበት ማዕከልና የገቢ ማሰባሰቢያ ሁሉገብ ሕንጻ ለመገንባት የሚያስችለውን 1 ሺህ 410 ካሬ ሜትር ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከበ።

ድርጅቱ የተረከበው ቦታ ለህሙማኑ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) አገልግሎት ለመስጠትና የገቢ ማሰባሰቢያ ተቋም ለመገንባት ያስችለዋል ተብሏል።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ያለምንም ክፍያ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኝ 1 ሺህ 410 ካሬ ሜትር ቦታ ለድርጅቱ አስረክቧል።

ይህም መንግሥት ለኩላሊት ሕሙማን የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው የሕንጻው ግንባታ ሲጠናቀቅ ድርጅቱ የራሱ የዲያሌሲስ ማዕከል እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከህንጻው ግንባታ ሱቆችን በማከራየትና ከኪራዩ በሚገኘው ገቢም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የኩላሊት ህሙማን መርጃ  የሚውል መሆኑን አረጋግጠው ይህም በየቦታው የሚስተዋለውን የኩላሊት ህሙማኑን የገንዘብ ልመና ለማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት።

ድርጅቱ በተረከበው ሥፍራ ከ17 እስከ 20 ወለል የሚደርስ ሕንፃ ከ4 እስከ 5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመገንባት ማቀዱንና እስከዛም ድረስ በቀላሉ ሊፈርሱ የሚችሉ ተገጣጣሚ ቤቶችን በመገንባት ለህመምተኞች አፋጣኝ የዲያሊሲስ ህክምና ለመስጠት አቅዷል ብለዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡና አጋር ድርጅቶች ለማዕከሉና ለገቢ ማሰባቢያ ሕንጻ ግንባታው እውን መሆን ከጎናቸው እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

በድርጅቱ በኩል ለአራት ዓመታት ያህል የዲያሊሲስ ተጠቃሚ የሆነችው አንችናሉ ገላው፤ መንግሥት ባደረገው ድጋፍ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።

ሌላዋ የኩላሊት ታማሚ ወጣት ብርቱካን ቢሳ በበኩሏ፤ በተደረገው ድጋፍ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ የማዕከሉ ግንባታ እንዲፋጠን ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም