ዩኒቨርስቲው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ በምርምርና ጥናት ለማገዝ እየሰራ መሆኑን አሰታወቀ

186

ባቱ ሚያዝያ 12/2014(ኢዜአ) የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዲፈታ በጥናትና ምርምር ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ባለው የሪፎርምና የአቅም ግንባታ ስራዎቹ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ  በየደረጃው ባሉ የመንግስት ተቋማት የመልካም አስተዳደር እጦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የህዝብ ብሶት የሚስተናገድበት ሆነዋል ብለዋል።

ችግሩ ውስብስብና የተለየ መፍትሔ የሚፈልግ ነው፤ በተለይ በህዝባዊ ውይይት ጎልቶ የወጡ ችግሮች እንዲፈቱ  በጥናትና ምርምር  የመፍትሔ አማራጮች ላይ በመስራት እናግዛለን ነው ያሉት።

አሁን ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን በተለመደው አሰራር መፍታት እንደማይቻል የተናገሩት ዶክተር ገረመው፤ አዳዲስ የማስፈፀሚያ ስልቶችና ስትራቴጂዎችን በጥናትና ምርምር በመለየት መንግስትን ለማገዝ እየሰራን ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በአመራሮች ዘንድ የሚታየውን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ውስንነት ችግር ለማቃለል የአቅም ግንባታ ስልጠና  "ማኑዋል"  እያዘጋጀ መሆኑንም ዶክተር ገረመው ተናግረዋል።

በዚህም  የአቅም ግንባታ፣ በተቋማዊ ሪፎርም፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር ስራዎች ከክልሉና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አዲስ ስትራቴጂ፣ የስርዓተ ትምህርትና ስልጠና "ማኑዋሎች " እና " ሞጁሎችን"  በፕሮፌሽናል የሰው ሃይል የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኩባ፣ ከናዳና ኬንያ ካሉ አቻ ተቋማት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር ውስጥ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለመፍታት ልምድ ለመለዋወጥ በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል ዶክተር ገረመው።

በተጨማሪም አቻ ተቋማቱ የደንበል ሃይቅ የእንቦጭ አረም ለማስወገድ በሚሰሩ ተግባራት ላይም እየተባበሯቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ከ50 በላይ በሆኑ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ያወሱት ዶክተር ገረመው፤ በፌዴራልዝምና ፖሊሲ ጥናት ደግሞ የሶስተኛ ዲግሪን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም