ፖሊስ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በገበያና ሌሎች ሥፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል

79

ሚያዚያ 12/2014/ኢዜአ/ ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በገበያና በሌሎች ሥፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።


የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ፖሊስ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

በተለይም የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው የገበያ ማዕከላትን ጨምሮ በመዝናኛ ሥፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ አስፈላጊው ክትትልና ጥበቃ እንደሚደረግ ነው የገለጹት።

በበዓላት ወቅት በርካታ ግዥና ሽያጭ ስለሚካሄድ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች በገበያው ሊሰራጩ ስለሚችሉ ኅብረተሰቡ እንዳይታለል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ የብር ኖት ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ አሁን ላይ ባንኮች ያቀረቡትን ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በመጠቀም ለወንጀል ድርጊት ተጋላጭነትን መቀነስ ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡም የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ኅብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ የወንጀል ድርጊቶች ሲመለከት በአካል ወይም በስልክ ቁጥር 011-1- 11-01-11 እንዲሁም 991 ነጻ የስልክ ጥሪ በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጥም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም