ጽንፈኝነትንና አግላይ አስተሳሰብን በመታገል ለሀገራችን ልማት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን- ወጣቶች

87

ሚዛን አማን፣ ሚያዝያ 12/2014 (ኢዜአ)ጽንፈኝነትንና አግላይ አስተሳሰብን በመታገል ለክልላቸውና ለሀገራቸው ልማት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ወጣቶች ተናገሩ ።

 የፈተናዎች ብዛት ከብልጽግና ጉዞ አያደናቅፈንም!” በሚል መሪ ሀሳብ  የብልፅግና ፓርቲ በአንደኛ ጉባዔው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ላይ የወጣቶች ውይይት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት አስማማው ከድር በሰጠው አስተያየት የትናንት አግላይነትና ጽንፈኝነት አስተሳሰብን በመሻገር በንጹህ ልቦና ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ልማት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

መንግስት በአካባቢው ህዝብን ይጠቅማሉ ተብሎ በርካታ ሀብት ፈሶባቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች መጓተትን ችግር እንዲፈታ ወጣት አስማማው ጠይቋል።

የቦንጋ የቡና መዚየም ሥራና የንጹህ መጠጥ ውሃ  ችግርን በመጥቀስ።

ክልሉ ባለው ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት የሀገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚቻልና  ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች ሊታሰቡ እንደሚገባ ያመለከተው ደግሞ ሌላኛው ወጣት ታረቀኝ ታከለ ነው።

አካባቢውን በማልማት የወጣቱን ሥራ አጥነት ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ጠቁሟል።

መንግሥት የመሠረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርገውን እንቅሰቃሴ በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የብልፅግና ፓርቲ የክልሉ የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት  ባርዱላ ኦልኪቦ፤  ፓርቲው የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጉባኤው የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ ማስቀመጡን ገልጿል።

ወጣት ብሩህ ተስፋና ህልም ያለው በመሆኑ ዛሬና ነገን አሻግሮ መመልከት የሚችል አቅም እንዳለው የተናገሩት አቶ ባርዱላ፤ "ወጣቱ ያለውን አቅም ተጠቅሞ የለውጥ ኃይል እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል" ብሏል።

ወጣቱ የትናንቱን በመርሳት፣ የዛሬን ፈተና በጽኑ ልቡናና በጠንካራ የስራ ባህል ግንባታ በተስፋ ብርሃን በማየት፣ በብርታትና አብሮነት መጻኢን ጊዜ በብልጽግና መሻገርን አልሞ እንዲንቀሳቀስ አሳስቧል።

የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ሊግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወጣት  ታሪኩ ታደሠ ፤ ወጣቶች ፓርቲው በጉባዔው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑና የሀገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲፋጠን የድርሻቸውን  ሊወጡ እንደሚገባ  ተናግሯል።

ፓርቲው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የወጣቶች የተቀናጀ ድጋፍ በሁሉም ዘርፎች እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

በመገፋፋት፣ በጽንፈኝነትና በአግላይነት እንዲሁም እኔ ብቻ  በሚል ስሜት ሀገር ሊገነባ እንደማይችል ነው ወጣት ታሪኩ የተናገረው።

አሁን እያጋጠመ ያለውን የምግብ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የተጀመረው "ምግቤን ከጓሮዬ" ንቅናቄ ላይ ወጣቱ በመሳተፍ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም