ምርታማነትን በሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ አሰራሮች ላይ ትኩረት ይደረጋል---የክልሉ ግብርና ቢሮ

193

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ሚያዚያ 11/2014 በመጪው የመኸር ወቅት የሰብል ምርታማነትን በሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻክል ወረዳ ምርታማነትን በሚጨምርና በአርሶ አደሮች እየተተገበረ ያለውን የተቀናጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ዛሬ አስጎብኝቷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀይለማሪያም ከፍያለው በወቅቱ እንደተናገሩት በክልሉ የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራስን ለመቻል ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የሰብል ምርታማነትን የሚያሳድጉ የኩታ ገጠም አስተራረስ፣ ትራክተር፣ ምርጥ ዘርና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት ለመጠቀም አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

"አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ በርሚንግ ኮምፖስት፣ ፍግ እና ፈሳሽ ማዳበሪያን በመጠቀም ላይ አተኩሮ እንዲሰራ እስከ ታች ድረስ በመውረድ ድጋፍና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል" ብለዋል።

ዘንድሮ ከገጠመው ችግር በመነሳት በአርሶ አደሩ ጉልበት የሚዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በዋናነት ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ዶክተር ሀይለማሪያም አመልክተዋል።

ሃላፊው እንዳሉት ማሳን ደጋግሞ በማረስ፣ በመስመር በመዝራትና የተባይና የአረም ክትትል በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የግብርና ባለሙያዎች የእለት ተእለት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

በጉብኝቱ በማቻከል ወረዳ አማኑኤል ዙሪያና ደብረቀለሙ ቀበሌዎች የሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች ያዘጋጁት የተቀናጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለሌሎች አርሶ አደሮች ተሞክሮ እንደሚሆን መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር ሃይለማርያም እንዳሉት በክልሉ ከ71 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን 31 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ተዘጋጅቷል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል በበኩላቸው እንዳሉት በ2014/2015 ምርት ዘመን በዞኑ ከ611ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረትን ለማቃለል እስካሁን ከ5 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ተጨማሪ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ነው።

በዞኑ ሦስት ወረዳዎች ተጀምሮ የነበረውን የበርሚንግ ኮምፖስት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በአሁኑ ወቅት በ17 ወረዳዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩ እየተዘጋጀ ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የገጠመውን ጊዜያዊ ችግር ለማቃለል ብቻ ሳይሆን የአፈርን ለምነትን ለማሻሻል፣ ወጪ ለመቀነስና የመሬትን እርጥበትን በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።

"በአርሶ አደሮች በመንደር ደረጃ የሚዘጋጀው ማዳበሪያ ለሌሎችም አስተማሪ ይሆናል" ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊና በጉብኝቱ የተሳተፉት አቶ ግዛቸው ጀምበሬ ናቸው።

በተሞክሮ ያዩት የማዳበሪያ ዝግጅት የገጠመውን የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ባጭር ጊዜ ለመቅረፍ ተስፋ የሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ ዞናቸው ሲመለሱ ተግባራዊ እንዲደረግ በሀላፊነት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በማቻከል ወረዳ አማኑኤል ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምረቱ አለማየሁ ለመኽር እርሻ ሥራቸው ከ34 ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ  ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለምርት ወቅቱ ከሚያስፈልጋቸው ስምንት ኩንታል የፋብሪካ ማዳበሪያ ውስጥ አራት ኩንታሉን እንደሚተካላቸው ገልለዋል ።

በአማራ ክልል በ2014/2015 ምርት ዘመን መኸር ወቅት 4 ነጥብ  8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም