በደቡብ ክልል በዓላትን ታሳቢ በማድረግ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለህብረተሰቡ እየተሰራጨ ነው

92

ሀዋሳ (ኢዜአ) ሚያዚያ 11/2014 በደቡብ ክልል ለመጪዎቹ የትንሳኤና የኢድ አልፈጥር በዓላት ገበያን ለማረጋጋት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እየተሰራጨ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ ወቅታዊ ሁኔታን እንዲሁም በዓላትን አስታኮ ያልተገባ የዋጋ ንረትና ውጥረት እንዳይከሰት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሀላፊው በመግለጫቸው  በበርካታ ከተሞች በተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ህብረተሰቡ በምሬት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የኑሮ ውድነት በዋናነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

በገበያው የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመከላከልና የሀዝብን ጥያቄ መመለስ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ በትንሳኤና በኢድ አልፈጥር በዓላት ገበያን ለማርገብ ዘይትና ስኳር በህብረት ሥራ፣ በሸማቾች ማህበራትና በግል ቸርቻሪዎች በኩል ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁን ወቅት ለክልሉ በኮታ የተመደበው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሊትር ዘይት ወደ ህብረተሰቡ የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስርጭቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ለእያንዳዱ ዞንና ወረዳ መዋቅሮች በህዝብ ቁጥር ልክ የተመደበውን የዘይት መጠን የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ስኳር በህብረተሰቡ ኮታ ልክ እየቀረበ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት እጥረት አልተከሰተም።

ቢሮው በበዓላት ወቅትም ሆነ ከበዓል ውጭ ባሉ ጊዜያት በምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩና የመሸጫ ዋጋ የማይለጥፉትን ለመቆጣጠር ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

"ለዚህም እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ ተቆጣጣሪ አካላት የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ይሰራል" ብለዋል።

ቢሮው ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል የሚሸጡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ለተጠቃሚ የሚያቀርቡና ህገወጥ ሥራ የሚሰሩትን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ማሄ ገለፃ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራት የተጠረጠሩ 33 ሺህ ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን  29 የንግድ ተቋማት ደግሞ ታሽገዋል።

ሌሎች 239 ነጋዴዎች በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጎ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

በተለይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉና ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች ከኢኮኖሚያዊ ጉዳታቸው ባሻገር በማህበረሰቡ ጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

ህብረተሰቡ ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩ፣ እንዲሁም ጊዜ ያለፈባቸውና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምርቶችን የሚያቀርቡ ሕገ-ወጦች ሲያጋጥሙት ለሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም