ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ40 ቢሊዮን ብር የኮንትራት ውል 50 የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ነው

239

ሚያዚያ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በሚጠይቅ የኮንትራት ውል 50 የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ በአቃቂ ቃሊቲ የሚገኘውን “የተገጣጣሚ ህንፃ ግንባታ ማምረቻ ማዕከል” ከፌደራል፣ ከክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።

ጉብኝቱ በኮንስትራክሽን ግብዓት ምርት እና ተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ቴክኖሎጂ ረገድ እየተካሄደ የሚገኘውን ውጤታማ ተሞክሮ ለማጋራት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ለከተሞች የቤት ግንባታ ልማት አጋዥ የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጎበኘው ማዕከል ለውሃ፣ ለቤት፣ ለትራንስፖርት፣ ለመስኖና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በ2014 በጀት ዓመት ከ40 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ የኮንትራት ውል የመስኖ መሰረተ ልማት፣ የመንገድ፣ የቤቶች ልማትና ሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ጨምሮ 50 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ኮርፖሬሽኑ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ የሰላም ችግሮች የመቀዛቀዝ አዝማሚያ ቢታይም ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄኖስ ወርቁ ኮርፖሬሽኑ እያካሄደው ያለው የግንባታ ምርት ኢትዮጵያ ሃብቶቿን በአግባቡ በመጠቀም እድገት ማረጋገጥ እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ የተጣሉ ሃብቶችን መልሶ በማምረት ለመጠቀም የጀመረው ጥረት ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ጥሬ እቃዎችን ለመተካት የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ተቋሙ ውጤታማ ለውጥ በማካሄድ በእጅ ያሉ ሃብቶችን በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ማሳየቱን ጠቅሰው፤ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በቀጣይም መሥራት የሚቻልበት እድል መኖሩን ማሳየቱን ገልጸዋል።

ሌላው የኦሮሚያ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጉዮ ገልገሎ የተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ጥሬ እቃ ምርቶች በክልላቸውም ሆነ በመላ ሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የቤት አቅርቦት ፍላጎት ለመሙላት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች በዝቅተኛ ወጪ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማከናወን የሚያስችል ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ