በሐረሪ ክልል የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት አውደ ርዕይ ተከፈተ

248

ሐረር ፤ ሚያዚያ 11/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል “በቴክኖሎጂ ፈጠራ የክልሉን ብልፅግና እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት አውደ ርዕይ ዛሬ በሐረር ከተማ ተከፈተ።

በሐረር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ተዘጋጅተው የቀረቡበት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕዩ ለሁለት ቀናት ለህዝብ ክፍት እንደሚቆይ ተገልጿል።

አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት የሐረሪ ክልል  ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም እና የሐረር  ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን   አቶ ሚልኬሳ አህመድ ጋር በመሆን ነው።

በዚህም  ችግር ፈቺ የሆኑ የበቆሎ መፈልፈያ ፣ኤሌክትሮኒክስ እና የጨርቃጨርቅ ማምረቻ የፈጠራ ስራዎች ቀርበውበታል፤ ዓላማውም ግኝቶችን በማስተዋወቅ ወደ ህብረተሰቡ ደርሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማነሳሳት እንደሆነ ተመልክቷል።

የምክር ቤቱ አፈ – ጉባኤ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ በአውደ ርዕዩ ላይ የክልሉ መንግስት በኮሌጁ የተጀመሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው ድጋፍ  እንዲያመቻች  ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ የሆኑ የስልጠናና የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን በማዳበርና በማበልፀግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ኮሌጁ የሚያከናውነውን የቴክኖሎጂ ስራ ለማጎልበት የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኮሌጁ ዲን በበኩላቸው፤ በተቋሙ  ውስጥ በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች የተዘጋጁ የፈጠራ ስራዎች በአውደ ርዕዩ ላይ መቅረባቸውን ገልጸዋል።

አወጭ የሆኑ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን በሚፈለገው መጠን ለማውጣትና  የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማሳካት እያደረጉ  ባለው እንቅስቅሴ ያጋጠማቸውን  የበጀት እጥረት ችግር ለመፍታት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለመሸጋገር በሂደት ላይ እንዳለም አቶ ሚልኬሳ ጠቁመዋል።

በአውደ ርዕዩ  ከተሳተፉት መካከል  በኮሌጁ የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር አሰልጣኝ መምህር ምስክር ሸዋንግዛው የበቆሎና ስንዴ መፈልፈያ ማሽን ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

የፈጠራ ስራው ካሁን ቀደም በእንስሳት እየታገዙ ከ10 በላይ ሰዎች  ይወቃ የነበረው ስንዴና ማሽላ በቴክኖሎጂው ፈጠራ የተገኘው ማሽን  በአንድ ሰው መሰራት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ይህም ጊዜና ጉልበት እንደሚቆጥብ ተናግረዋል።

ሌላው  በኮሌጁ ሰልጣኞች ፈጠራ  የተሰራው  የሎዝ መፈልፈያ ማሽን  ካሁን ቀደም ሎዝ ለመፈልፈል ይባክን የነበረውን ጊዜና ጉልበት እንደሚቀንስ ተመልክቷል።