በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደቀያቸው ይመለሳሉ

918

አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ሙሉ በሙሉ  ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ብሄራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ተጎጂዎችን ወደ ቀያቸው በመመለሱ ረገድ ህብረተሰቡ፣ የልማት አጋሮችና የክልል መንግስታት ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ደመና ዳሮቴ ለኢዜአ እንዳሉት በዚህ ዓመት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ግጭትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

“ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፤ የተለየ ምክንያት ካልገጠመ በቀር ቀሪዎቹም በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ” ብለዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ መርሐ ግብር ነድፎ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት በምዕራብ ጉጂ ዞን በ26 ጣቢያዎችና በጌዶኦ ዞን በ77 ጣቢያዎች ተጠልለው የነበሩት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በበቅርቡ ወደ ቀያቸው ከተመለሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በሶማሌ ክልል ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ  በመንግስትና በህብረተሰቡ ትብብር የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየ ቀዬአቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት በጅግጅጋ የነበሩት ሙሉ በሙሉ የተመለሱ ሲሆን በጭናግሰን፣ በባቢሌና በቀብሪ ደሀር እንዲሁም በሌሎቹም አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው በመመለስ ላይ ናቸው።

ከጎረቤት አገር ጅቡቲም የተፈናቀሉ 6 ሺህ 418 ሰዎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል።

የጌዲኦና የጉጂ ዞኖች ጉዳይ በአሁኑ ወቅት መፍትሔ በማግኘቱ  ከአካባቢዎቹ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀዬቸው መመለስ ጀምረዋል።

በግጭት ምክንያት በርካታ ሰው ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለበት ጊዜ አሁን ቢሆንም ችግሩ ግን ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነ ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት።

ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የህዝብ ለህዝብ፣ የደህንነትና የፀጥታ እንዲሁም የሰላም ኮሚቴዎችን በማዋቀርና በየቀበሌዎቹ ውይይቶችን በማካሄድ የታገዘ ነው።

በዚህ ረገድ መንግስት፣ አጋር አካላት እና ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ አንስቶ ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው እስኪመለሱ ድረስም ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውን አቶ ዳማና አስታውቀዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና ተጎጂዎችን በማገዝ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳሰበዋል።

መንግስት በበጀት ዓመቱ በአገሪቱ በቋሚነት ድጋፍ ከሚያሻቸው ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተጨማሪ በግጭት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፣ በጎርፍ አደጋ ደግሞ ከ2 ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ እርዳታ አድርጓል።