የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይት ዎች የጋራ ሪፖርት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያጋለጠውን የወልቃይት ጅምላ ጭፍጨፋ ለመሸፈን ያለመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይት ዎች የጋራ ሪፖርት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያጋለጠውን የወልቃይት ጅምላ ጭፍጨፋ ለመሸፈን ያለመ ነው

ሚያዚያ 9/2014/ኢዜአ/ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይት ዎች የጋራ ሪፖርት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያጋለጠውን የወልቃይት ጅምላ ጭፍጨፋ ለመሸፈን ያለመ ነው ሲል አሜሪካዊው የፎቶ ጋዜጠኛ ጀማል ኮንቴስ ተናገረ።
አሜሪካዊው የፎቶ ጋዜጠኛ ጀማል ኮንቴስ ባለፈው ሳምንት በወልቃይት አካባቢ ባደረገው ጉብኝት በርካታ የጅምላ መቃብር መመልከቱን ለኢዜአ ተናግሯል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይት ዎች የመንግሥት ኃይሎች በወልቃይት ወንጀል እንደፈጸሙ አስመስለው ሪፖርት ማውጣታቸው እጅግ አሳዝኖኛል ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ ተቋማት ያወጡት የጋራ ሪፖርት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕወሓት በወልቃይት የፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ያቀረበውን የጥናት ግኝት ለማጣጣል ያለመ መሆኑን ተናግሯል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ባደረጉት ምርምር የሕወሓት አምባገንን አገዛዝ ባለፉት 40 ዓመታት በወልቃይት፣ ጸገዴና ጸለምት አካባቢ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን በመጨፍጨፍ የቀበረበትን የጅምላ መቃበር ማግኘታቸውን መረዳቱን ገልጿል።
ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉት ሁለቱ ተቋማት ይህንን እውነታ ወደጎን በመተው ሪፖርት ማውጣታቸውን ጠቅሶ ሪፖርቱም የፖለቲካ ፍላጎትን ያዘለ ነው ብሏል።
የተቋማቱ የጋራ ሪፖርት በወልቃይት የተገኘውን የጅምላ መቃብር አስመልክቶ ገሃድ የወጣውን የምርመራ ውጤት ጥላሸት ለመቀባት ያለመ መሆኑን አስረድቷል።
በወልቃይት ባደረገው ጉብኝት፤ የአካባቢው ነዋሪዎች የጠፉ ዘመዶቻቸውን አስክሬን ከጅምላ መቃብር ውስጥ ለመለየት በእጃቸው ጉድጓዱን ሲቧጥጡ መመልከቱን ገልጾ ኩነቱ አሳዝኖኛል ብሏል።
“እነዚህ ሁለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ተቋማት እውነታውን በመካድ በራሳቸው መንገድ ሪፖርት አውጥተዋል፣ይህ ጥረታቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን ሪፖርት እውነታ ለማደብዘዝ ያለመ ነው” በማለት ተናግሯል።
እንዲያም ሆኖ በዚህ ሪፖርትና በምዕራባውያኑ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማሳሳት ጥረት መደረጉንም ነው ጋዜጠኛው ያነሳው።
ይህም ምዕራባውያኑ ሕወሓት የፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በተመለከተ ያለውን እውነታ መስማት ካለመፈለግ የመነጨ የሃሰት ሪፖርትና ዘገባ መሆኑን በመጠቆም።