ሀሰተኛ የምስክር ወረቀት ህትመትን ለመከላከል የሚረዳ ማተሚያ ከሰኞ ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል

80

ሚያዝያ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)ሀሰተኛ የምስክር ወረቀት ህትመትን ለመከላከል የሚረዳ 'ሴኩርዩርድ ፕሪንተር' የተባለ ማተሚያ ከሰኞ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል የአዲስ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ማተሚያው በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ለሰራተኞች ገለጻና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ እንደተናገሩት፤ በኤጀንሲው አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የሚሰራጩ 150 ዘመናዊ ማተሚያ መሳሪያዎች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል።

ከተገዙት ውስጥ 127 የሚሆኑት አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው ቀሪዎቹ ማዕከል ላይ እንዲቀመጡ መደረጉን አብራርተዋል።

ማተሚያው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም በመሆኑ ሀሰተኛ የምስክር ወረቀቶች እንዳይታተሙ ከማስቻሉም በላይ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ማተሚያ መሳሪያው ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችና ከውጭ በመጡ ሙያተኞች መካከል የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ከክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለተውጣጡ 200 የኤጀንሲው ሰራተኞች ስለመሳሪያው አተገባበር ገለጻ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ይህም ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ ሲውል ችግር እንዳያጋጥም በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ በበኩላቸው ማተሚያ መሳሪያው ወደ ሥራ መግባቱ በኤጀንሲው የሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ማተሚያው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።

ኤጀንሲው ለዜጎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም