የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ እንዲደርሱ ያደረገውን ጥረት አሜሪካ አደነቀች

408

ሚያዚያ 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 50 ተሽከርካሪዎች መቀሌ እንዲደርሱ ያደረገውን ጥረት አድንቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች 1 ሺህ 700 ሜትሪክ ቶን የሰብዓዊ እርዳታ መቀሌ እንዲደርስ ጥረት ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር የሚገኙ እና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረትም አድንቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ያደረገውን የግጭት ማቆም ውሳኔም የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሂደቱ ለሰላም አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልፀዋል።

አፋር ክልልን ጨምሮ በችግር ላይ ለሚገኙ ሁሉም ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።ሂደቱ ሰላምን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሁሉን አሳታፊ ለሆነ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሜሪካ ከ1 ሺህ 700 ሜትሪክ ቶን በላይ ሕይወት አድን የሰብአዊ ድጋፍ የያዙ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል መድረሳቸው በበጎ ጎኑ እንደምታየው አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሕወሓት በአፋር ክልል ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣና በዚህ ረገድም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በቡድኑ ላይ ጫናና ግፊት እንዲያደርግ በመግለጽ ላይ ይገኛል።

በሌላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው የተጓዙ 50 እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም መግለጹ የሚታወስ ነው።ከጫኑት እርዳታ ውስጥ ስንዴ፣የቅባት እህልና ነዳጅ እንደሚገኝበት ጠቁሟል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም