በሰሜን ጎንደር ዳባት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመዋል በሚል የተሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው

280

ሚያዚያ 06/2014 (ኢዜአ) በሰሜን ጎንደር ዳባት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሟል በሚል በአንዳንድ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ሀሰት መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ገለጸ።

በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የመጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች በአሸባሪው ህወሃት መልከ ብዙ ጥቃት ደርሶባቸው አካባቢውን እንዲለቁ መደረጉ ይታወቃል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት መጀመሪያ ማይጸብሪ በተባለው ስፍራ ቀጥሎም በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ በማዘጋጀት እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።

በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ስደተኞቹ በዳባት “አለም ዋጭ” ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በአንፃራዊነት በጥሩ ሁኔታ እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ስፍራዎች የነበሩ ስደተኞችም ወደ መጠለያ ጣቢያው እየገቡ መሆኑን ገልፀው በአንድ ወር ብቻ ከ4 ሺህ 800 በላይ ስደተኞች ወደ መጠለያ ጣቢያው ገብተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ከሰሞኑ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰሜን ጎንደር ዳባት የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በታጣቂዎች ጥቃት ተፈፅሟል በሚል ያሰራጩት መረጃ “ሀሰት” መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዙሪያ በቢቢሲ አማርኛ የተሰራጨ መረጃ እንደነበር አስታውሰው እውነታው በስደተኞች መካከል ተከስቶ የነበረውን የቡድን ጸብ ተከትሎ የተፈጠረ ግርግር ሆኖ ሳለ በእውነታው ላይ ያልተመሰረተ ዘገባ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ሚዲያዎች በምንጭነት ለተጠቀሙት ድርጅት ቅሬታ አቅርበናል ብለዋል።የድርጊቱን ሁኔታ በማስመልከት ዝርዝር መረጃ በምርመራ ላይ በመሆኑ ሲጠናቀቅ መረጃ እንሰጣለን ያሉት አቶ ተስፋሁን፤ ግርግሩ በሚዲያው እንደተባለው ሳይሆን የቡድን ጸብ ነው ብለዋል።

በዚህም አምስት ሰዎች ቆስለው ሶስቱ ቀላል ህክምና ተድርጎላችው ወደ ካምፕ ሲመለሱ ሁለቱ አሁንም ህክምና እየተደረገላችው መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ/ዶቼቨሌ/ በስደተኞች ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል በሚል ያሰራጨው ዘገባ ሀሰት መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በስደተኝነት ስም ሌላ አጀንዳ ፈጥረው ተጠቃሚ ለመሆን ተልዕኮ ያላቸው ካሉ እየተጣራ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።

ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለበት ሰላምና ደህንነታቸውን ይጠብቃል ነው ያሉት።

አገልግሎቱ ከዓለም አቀፉ ስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን እና የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በስደተኞች ጉዳይ ከሚሰሩ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለስደተኞች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጥር 1951 ስደተኞችን የመቀበል ግዴታ ገና በዓለም አቀፍ ሕግ ሳይደነገግ ኢትዮጵያ የታሪኳ አካል አድርጋ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት የመጡ የየመን መነኩሴዎችን እንዲሁም የነብዩ መሃመድ መልእክተኞችን መቀበሏን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በሕግ ደረጃም በ2011 ዓ.ም በወጣው አዋጅ የስደተኞችን የመዘዋወር፣ በጋራ ፕሮጀክቶች የማሳተፍ፣ ወሳኝ ኩነት አገልግሎት የመስጠትና የባንክ አገልግሎትን እንደፈቀደችና በስደተኞች አቀባበል ምስጉን ስም ያላት መሆኗን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንን ጨምሮ ከ24 አገራት ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች በ25 የመጠለያ ጣቢያዎች እየተስተናገዱ ይገኛሉ ብለዋል።