ባለፉት ሁለት ቀናት 50 ምግብና ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ ትግራይ ክልል ተልከዋል

337

ሚያዚያ 6/2014 (ኢዜአ) መንግስት በትግራይ ክልል እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ በተገቢው መንገድ እንዲደርስ ለማስቻል የግጭት ማቆም ውሳኔን ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

ይህንን ተከትሎም የሰብአዊ እርዳታን ወደ ክልሉ ለማድረስ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።

ከእነዚህም መካከል በየቀኑ የሚደረግ የአየር ትራንስፖርትን በማመቻቸት የእርዳታ አቅራቢ ተቋማት አቅም የፈቀደውን ያህል የመድሃኒት፤ የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ እንዲያጓጉዙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።

በየብስ ትራንስፖርትም በመጀመሪያው ዙር የምግብ ድጋፍን የያዙ 21 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ተደርጓል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ደግሞ 47 የምግብ ድጋፍ የያዙና 3 ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በድምሩ 50 የጭነት መኪኖች ከሰመራ ተነስተው ወደ መቀሌ ጉዞ እያደረጉ ነው።

ተጨማሪ 10 የምግብ እርዳታን የያዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችም ከሰመራ ጉዞ ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ለማድረግ የገባውን ቃል በማክበር ምቹ የሰብአዊ ርዳታ ማጓጓዣ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን መንግስት ያቀረበውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ትግራይ የሚደርሰውን የእርዳታ መጠን ከፍ ሊያደርግ ይገባል።

በሌላ በኩል በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ የሚገኙት የክልሉ ዜጎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ወራሪው ሃይል አሁንም ከያዛቸው የአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣና ምቹ የእርዳታ ማስተላለፊያ መስመርን መዘርጋት እንዲቻል አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያደርግ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም