በዞኖቹ ከ577ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ይሰጣል

426

ጊኒር፣ ግምቢ ሚያዝያ 6 /2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ፣ ምእራብ ና ቄሌም ወለጋ ዞኖች እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ለ577 ሺህ 717 ህጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ በዘመቻ እንደሚሰጥ የየዞኖቹ ጤና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

በዞኖቹ ክትባቱ ከነገ ሚያዝያ 7 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ዘመቻ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

የምስራቅ ባሌ ዞን ጤና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ጥለሁን ተካ ለኢዜአ እንደገለጹት የክትባት ዘመቻው በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 169 የገጠር ቀበሌዎች ይካሄዳል።

ክትባቱ  ለ137 ሺህ 717 ህጻናት እንደሚሰጥ ጠቁመው በዘመቻው 1ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች፣ ሱፐርቫይዘሮችና መንገድ መሪዎች እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ287 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ በዞኑ ጤና ጢበቃ ጽህፈት ቤት የህብረተሰብ ጤና ባለሙያ አቶ ገመቺስ መንገሻ ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ ከነገ ጀምሮ  በ21 ወረዳዎች ቤት ለቤት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን  አመላክተዋል ።

ክትባቱ ከ151ሺህ በላይ ለሚሆኑ  ህፃናት እንደሚሰጥ  የገለጹት ደግሞ የቄሌም ወለጋ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታምራት አለማየሁ ናቸው።

ህብረተሰቡ  ክትባቱ ቤት ለቤት መሆኑን ተገንዝቦ ልጆቹን እንዲያስከትብ ሃላፊዎቹ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም