ጀርመን በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎዋን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትሰራለች

96

ሚያዝያ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ)   ጀርመን በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎዋን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ገለጹ።

የሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪካ ንግድ ትርዒት ከሚያዝያ 24 እስከ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል መካሄዱን በማስመልከት ገለፃ ተደርጓል።

የሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪካ ንግድ ትርዒት ተቀማጭነታቸውን ጀርመን እና ኬንያ ባደረጉ የትሬድ ኤንድ ፌርስ ግሩፕ እና በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ አዘጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል።

በንግድ ትርዒቱ አፍሪካውያን የንግድ ወኪሎች፣ ነጋዴዎችና አምራቾች የሚያታደሙ ሲሆን ለአፍሪካ ገበያ ታቅደው የተዘጋጁ ጥራት ያላቸው ምርት እና አገልግሎቶች ይቀርባሉ ተብሏል።

በተጨማሪም ከ150 በላይ አምራችና ላኪዎች ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አፍሪካዊ የንግድ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች እና ሌሎች አካላትም የምርትና የፈጠራ ክህሎት ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ይጠበቃል፡፡

ከሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪካ ንግድ ትርዒት ጎን ለጎን የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በሁለትዮሽ ግንኙነቶች የመወያየት እድልን እንደሚያገኙ ተነግሯል።

በርካቶች እንደሚጎበኙት በሚጠበቀው የንግድ ትርዒት በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የአፍሪካ ገበያ የማሳደግ እድል ይፈጥራል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር፤ አፍሪካ ያላትን ጸጋ ተጠቅማ የመበልጸግ ከፍተኛ አቅም ያላት አህጉር መሆኗን ገልጸዋል።

አህጉሪቷ ዜጎቿን ተጠቃሚ እንድታደርግ ጀርመን በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅሰው ጀርመን በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎዋን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትሰራለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

በትምህርትና ስልጠና፣ በጤና፣ ስራ እድል ፈጠራ፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ጀርመን ከአፍሪካ ጋር በትኩረት እንደምትሰራም ተናግረዋል።

የንግድ ትርዒቱና ባዛሩ ለአፍሪካ የገበያ ፍላጎት አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡ ሁነኛ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔዎችን እንደሚገኙበት አመላክተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቱሪዝም መስክ ካስከተለው ጉዳት ለማገገም የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ታላላቅ ኮንፈረንሶችን ማካሄዷን አስታውሰው ይህም በመዲናዋ ለሚገኙ የሆቴልና አገልግሎት ዘርፎች መነቃቃት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

የእንጦጦ፣ ወዳጅነት እና አንድነት ፓርክ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለእንግዶች ምቹና ተጨማሪ መስህብ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ወንጪ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ አቅም እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በጀርመን ኤምባሲ አዘጋጅነት የሚካሄደው  የሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪካ ንግድ ትርኢትም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብት በማስተዋወቅ ከፍተኛ የገበያ ትስስርን የመፍጠር እድል ይኖረዋል ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ፤ ጀርመን በትምህርትና ስልጠና ዘርፎች የምታደርገው ድጋፍ ለአፍሪካ ልማት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

የሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪካ ንግድ ትርኢትም ለአህጉሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚፈጥር አንስተዋል።

ጀርመን የአፍሪካዊያንን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ እያደረገች የምትገኘውን ድጋፍም አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል።

በንግድ ትርዒትና ባዛሩ የቤት መኪኖች፣ መለዋወጫዎች፣ የኢንዱስትሪ ማሽኖች፣ የታዳሽ ኃይል አገልግሎት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የባንክ እና የገንዘብ ነክ አገልግሎቶች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ ትምህርት፣ ሥልጠና እና ሌሎች ዘርፎችም አገልግሎቶች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም