በአዲስ አበባ ከተማ ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑ ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩ ውስጡን በአግባቡ ሊፈትሽ ይገባል

399

ሚያዚያ 6/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑ ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ መዋቅሩ ውስጡን በአግባቡ ሊፈትሽ እንደሚገባ ተመላከተ።

"የአዲስ አበባን ሰላም ለማረጋገጥ ምን ይደረግ" በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ውይይት ተካሂዷል።  

በውይይቱም ላይ ህዝቡን ለምሬት እየዳረጉ ያሉ ወንጀሎች በዘላቂነት መከላከል የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም ነው የተነሳው።    

አስተያየት ከሰጡት መካከል አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ኤልሳቤት ተፈራ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል ናቸው።  

"ዘይት እየተሸሸገ ነው፣ ፎርጅድ ብሮች ታትመው ወደ ገበያው እየገቡ ነው" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በመናፈሻና መዝናኛ ቦታዎች በርካታ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣው ዝርፊያና ንጥቂያ በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ በለጠ ዘውዴ ናቸው።     

በተለይ የት አካባቢ ነው ወንጀል የሚሰራው?፣  ምን ሊሰራ ይገባል፤ የሚለው በሚመለከተው አካል በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።   

እንደ አቶ በለጠ ገለጻ የህዝቡን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥ በየአካባቢው የተዋቀረውን ህዝባዊ የጸጥታ ኃይል በወንጀል መከላከል ላይ ማሰልጠንና አቅም መገንባት አስፈላጊ ነው።  

"የጸጥታ አካላት ለህግ የበላይነት ተገዥ አለመሆን እንዲሁም ለገቡት ቃል ታማኝ አለመሆን ሌላው ችግር ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የንጉስነሽ ጌታነህ ናቸው።   

በሌላ በኩል ብሄርንና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ በመሆኑ ቸል ሊባል እንደማይገባ ያመለከተው ደግሞ ወጣት ስለሺህ ረበበ ነው።

በውይይቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤ ባለፉት ስምንት ወራት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች ሦስት በመቶ መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል።    

"በበጀት ዓመቱ 10 በመቶ ወንጀል ለመቀነስ እቅድ ከመያዙ አኳያ የተገኘው ውጤት በቂ አይደለም" ያሉት ኮሚሽነሩ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማግኘት የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ፖሊስ ወንጀሎችን ለመከላከል በእቅድና በተደራጀ መንገድ የመከላከል ስራው ላይ ትኩረት መስጠቱን በመጠቆም።  

ከሥነ ምግባር ችግር ጋር በተያያዘ 219 ፖሊስ አባላት ሙሉ በሙሉ የተሰናበቱ ሲሆን 417 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳያቸው በከባድ የሥነ ምግባር ጥሰት እንዲታይ መደረጉን ተናግረዋል።    

በተለያዩ ደረጃ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ በተሰራው ስራም 41 ሺህ የሚሆኑት ላይ ክስ የተመሰረተ ሲሆን 16 ሺህ በግዜ ቀጠሮ 1 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ በበኩላቸው ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ እንዲሰራ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በቀጣይም የከተማው ሕዝብ በየአካባቢው ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን በቅርበት እንዲከታተል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም