የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ የውጭ ምንዛሬ ቅድመ ክፍያ ባለመፈጸሙ በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ አይደለም

360

ሚያዚያ 6/2014 (ኢዜአ) የአደይ አበባ ስታዲየም ሁለተኛ ምእራፍ ግንባታ የውጭ ምንዛሬ ቅድመ ክፍያ ባለመፈጸሙ በተያዘለት ጊዜ እየተከናወነ አለመሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በስታዲዮሙ በመገኘት የግንባታ ሂደቱን ተመልክተዋል።

የስታዲየሙን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ በ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር ወጪ በ900 ቀናት ለማጠናቀቅ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ውል ተፈጽሞ ነበር።

በእቅዱ መሰረት በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሰራሽ ሀይቅ ግንባታ ይከናወናል።

እንዲሁም የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት፣ የተጫዋቾች የመለማመጃ ሜዳ እና ሌሎችንም የሁለተኛው ምእራፍ ግንባታ አካል ናቸው።

የግንባታው መጠናቀቂያ ጊዜ ከስድስት ወራት ያነሰ ጊዜ የቀረው ቢሆንም እስካሁን የተከናወነው ከእቅዱ ከግማሽም ያነሰ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው፤ አሁን ላይ የጣሪያ ተሸካሚ ምሰሶ ስራ፣ የውስጥ ክፍል ቀለም ቅብና የመለማመጃ ሜዳና ሌሎችም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አጠቃላይ በሁለተኛው ምእራፍ ግንባታ ከእቅዱ አንፃር ከ50 በመቶ ያነሰ መሆኑን ጠቁመው ለኮንትራክተሮቹ የውጭ ምንዛሪ ቅድመ ክፍያ አለመፈጸሙ ለግንባታው መጓተት ዋነኛው ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ግንባታውን የሚያከናውነው ኩባንያ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ለማስገባት ችግር የገጠመው መሆኑን ተናግረዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ስፖርት ዘርፍ  ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ የብሄራዊ ስታዲየሙ የግንባታ ሂደት ችግር እያጋጠመው መሆኑን ገልጸዋል ።

በመሆኑም ችግሩን በመፍታት ግንባታውን ለማፋጠን ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልገዋል ነው ያሉት።

ከስታዲየሙ የመስክ ምልክታ ቀደም ብሎ በ2012 ዓ.ም ስታዲየሙ ላይ ያጋጠመው የኦዲት ግኝት ማስተካከያ መደረጉን በተመለከተ ቋሚ ኮሚቴው ከሚኒስቴሩ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ፤ የከፍተኛ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግባቸው መሆን አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም የብሄራዊ ስታዲየሙ ግንባታ ህዝብ ለአገልግሎት የሚጠብቀው ፕሮጀክት በመሆኑ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም ቋሚ ኮሚቴው በስታዲየሙ ግንባታ የሚስተዋሉ የኦዲት ግኝቶችን በመለየት እንዲያስተካከል አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

የባህል ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ከፍተኛ አመራሩ የኦዲት ግኝት መኖሩን እንደማያውቅ ገልጸው ችግሩን ለማየት ተጨማሪ ቀን እንዲሰጥ በመጠየቃቸው ቋሚ ኮሚቴው ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ ይዟል።

በቻይናው ስቴት ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ግንባታው እየተከናወነ ያለው ይህ ስታዲየም  የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት የተከናወነ ሲሆን የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ 5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በላይ ይወስዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም