በመዲናዋ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ያላቸውን ንብረት በአግባቡ እየተጠቀሙና እያስተዳደሩ አይደለም

95

ሚያዝያ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በመዲናዋ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ያላቸውን ንብረት በአግባቡ እየተጠቀሙና እያስተዳደሩ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ባለስልጣኑ የበጀት አመቱን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻፀም አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ጊዜ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ ኢብራሂም፤ በርካታ ተቋማት ያላቸውን ንብረቶች በአግባቡ ከማስተዳደር አኳያ ክፍተቶች እንደሚስተዋልባቸው ተናግረዋል።

በተቋማቱ ያላለቁና ጥቅም እየሰጡ የሚገኙ ንብረቶች እያሉ ተጨማሪ የመግዛት አካሄዶች እንዳሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተቋማት ተጠያቂነት ያልሰፈነበትና ተገቢ ያልሆነ የንብረት አወጋገድ ስርአት መኖሩን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

የንብረት ማዘዋወር እና አጠቃቀም ሂደቱ ክፍተት ያላበት ከመሆኑ ባለፈ ለብክነትና ለስርቆት የተጋለጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አሁን እየተስተዋለ ያለው አካሄድ በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚገዛው ሀብት በከንቱ እየጠፋ መሆኑን አመላካች ነውም ብለዋል።

ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ የመንግስት ተቋማት የሚጠቀሙበት የ4 ሺህ 80 ህንጻዎች መኖራቸውን በቆጠራ ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ የ3 ሺህ 620 ህንጻዎችን የእርጅና ቅናሽ በማስላት ግምታዊ ዋጋቸውን 22 ነጥብ 3 ቢልዮን ብር መሆኑን ባለስልጣኑ መዝገቧል ብለዋል።

በንብረት ዘርፍም የ675 ተቋማትን ንብረት በመመዝገብ አጠቃላይ ዋጋቸውን መሰላቱን ተናግረዋል።

አያይዘውም ሊወገዱ የነበሩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ተጠግነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ 19 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የመንግስት ሀብት ማዳን መቻሉን አቶ የሱፍ አስታውቀዋል።

ባለቤት የሌላቸውን ንብረቶች በመለየት እና በጋዜጣ ማስታወቂያ እንዲወጣ በማድረግ ባለቤት ያልተገኘላቸውን ንብረቶች ባለስልጣኑ ተረክቦ ማስተዳደር መጀመሩንም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ በስሩ የሚገኙ መስሪያ ቤቶችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ከቢሮ ኪራይ ነጻ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በየአመቱ እስክ አንድ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ለቢሮ ኪራይ ወጪ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

የባለስልጣኑ የእቅድና በጀት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ አለሙ በበኩላቸው የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም 94 በመቶ መሆኑን አንስተው በቀጣይ ብዙ ስራዎች እንደሚጠበቁም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ንብረቶችን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል ስታንዳርድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተቋማት ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን ለመመዝገብ፤ ፍሰቱን ለመቆጣጠር በተገቢው መልኩ ኦዲት ለማድረግ፤ ንብረቱ የትና በማን እጅ ነው ያለው የሚለውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለማበልፀግ ማቀዱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም