የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰብአዊ እርዳታ ከውጭ ለገባ ቁሳቁስ የመጋዘንና የአገልግሎት ክፍያ ወጪ ሰረዘ

380

ሚያዝያ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእርዳታ ለገቡ ቁሳቁሶች የመጋዘን ኪራይና የአገልግሎት ክፍያ ይውል የነበረ 25 ሚሊዮን ብር ወጪ መሰረዙን አስታወቀ።

አየር መንገዱ በካርጎ መጋዘን የተከማቹ የድጋፍ ቁሳቁሶችንም በዛሬው እለት ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክቧል።

በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ ከስራው ጎን ለጎን በማህበራዊ ሃላፊነትም የላቀ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድርቅና ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የሚደርስ 114 ሺህ 400 ኪሎ ግራም የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች መላኩን ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱም የድጋፍ ቁሳቁሶቹን በመረከብ በጭነት ማከማቻ መጋዘኖች ሳይበላሹ ጥራታቸው እንደተጠበቁ እንዲቆዩ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ለቁሳቁሶቹ የመጋዘን ክፍያን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ይጠየቅ የነበረውን ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አየር መንገዱ መሰረዙን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አይድሩስ ሀሰን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላደረገው ቀና ትብብርና ማህበራዊ ሀላፊነት አመስግነዋል።

የእርዳታ ቁሳቁሶቹም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በፍጥነት ተደራሽ የሚደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለማጠናከር በማሰብ ''ኢቲ ፋውንዴሽን'' ማቋቋሙ ታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም