ቋሚ ኮሚቴው ንብረቶች ከወደብ በወቅቱ እንዲነሱ አሳሰበ

142

ሚያዝያ 06/2014 (ኢዜአ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሞጆ ደረቅ ወደብ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

በምልከታውም ንብረቶች በወደብ ከሚቆዩበት የጊዜ ገደብ በላይ መቆየታቸው ባለንብረቶችንም ሆነ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ ንብረቶች ከወደብ በወቅቱ እንዲነሱ ጠንከር ያለ የአሰራር ስርአት ሊዘረጋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በሞጆ ደረቅ ወደብ የወደብ እና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረት-አብ ተክሉ በወደቡ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ሲያስረዱ በአሁኑ ሰአት በውርስ ምክንያት መሰብሰብ ካለባቸው 36 በመቶ ያህሉን ብቻ እንደሚሰበስቡ አንስተዋል፡፡

በወደቡ በአማካይ ከሶስት ሺህ በላይ ኮንቴነሮች ከአስራ አምስት ቀን በላይ የሚቆዩ እንደሆኑ ነው ያስረዱት፤ በመሆኑም ከህግ ማእቀፍ አኳያ እነዚህ ከባድ ችግሮች የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው በአዋጁ ተፈጻሚነት ዙሪያ ያለውን የድጋፍ እና ክትትል ስራ ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት እንደሚሰራበትም ነው የጠቆሙት፡፡

ንብረቶች በወደብ በቆዩ ቁጥር ያለ አግባብ የገንዘብ ብክነት ውስጥ እንዳይገቡ ለባለንብረቶች በማስገንዘብ እና እቃዎችን በጊዜ እንዲያነሱ አስገዳጅ ህጎችን በማሻሻል እና የተደራጀ መረጃ በማቅረብ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ያሰፈልጋል ብለዋል፡፡

አክለውም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትልቅ ሚና እንዳለው ማስረዳታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም