ማህበሩ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሩዝ ድጋፍ አደረገ

122

ሐረር ሚያዚያ 5/2014 (ኢዜአ )ማርክል ላየን ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በምሰራቅ ሐረርጌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሩዝ ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ ተወካይ አቶ ኡመር ኡስማኢል ድጋፉን ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር ዛሬ አስረክበዋል ።

በብልጽግና ፓርቲ የምሰራቅ ሐረርጌ ዞን  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዲ አልይ ድጋፉን ሲረከቡ  እንዳሉት የህዝብ ለህዝብ ድጋፉ  በዞኑ  ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ  በተከሰተ ድርቅ ዜጎች ለችግር እንዳይጋለጡ ጉልህ አስተዋጾ አበርክቷል።

"ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎችና ተቋማት እየተደረገ ያለው ድጋፍ  በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ማህበረሰቡ  ከቀየው እንዳይፈናቀልና  ለረሃብ እንዳይጋለጥ  እገዛ አድርጓል" ብለዋል።

ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ ያመሰገኑት ሃላፊው ሁሉም አካላት ለተጎጂዎች እያደረጉ ያለውን ድጋፍ  አጠናክረው እንዲቀጥሉ  ጥሪ አቅርበዋል ።

የማህበሩ ተወካይ አቶ ኡመር ኡስማኢል በበኩላቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን አርብቶ አደሩ በሚኖርባቸው ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሩዝ  ድጋፍ  መደረጉን  ተናግረዋል።

ማህበሩ የህዝብ ለህዝብ መረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶችን በማጎልበት ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እየተደረገ  ባለው ሁሉንአቀፍ  ርብርብ እስካሁን  የከፋ ችግር አለመድረሱን የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኑሬ መሀመድ ናቸው።

ከባለሃብቱ፣ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ከለጋሽ ድርጅቶችና ከህብረተሰቡ ከ9ሺ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ድጋፍ ለተጎጂዎች መከፋፈሉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም