በዋግ ኸምራ በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 2ሺህ 695 ተማሪዎች ትምህርት እየተሰጠ ነው

94

ሰቆጣ ሚያዝያ 5/2014 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 2ሺህ 695 ተማሪዎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመጠለያ ጣቢያዎች የትምህርት ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ፋንታየ ለኢዜአ እንዳሉት በአሸባሪው ህወሓት ወረራ  ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ጥረት እየተደረገ ነው።

እስካሁን 2ሺህ 695 ተማሪዎች በመደበኛና በ10 ጊዜያዊ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተባባሪው እንዳሉት ከተማሪዎቹ ውስጥ 1ሺህ  የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የአንደኛ ደረጃና የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ናቸው ።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) ለወለህ መጠለያ ጣቢያ በለገሳቸው ስምንት ድንኳኖች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

መምሪያው በወለህ መጠለያ ጣቢያ ለተዘጋጀ ጊዜያዊ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መቀመጫዎች በማሟላት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በትምህርት ቤቱ ከተማሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የገጠመውን የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለማቃለል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የወለህ መጠለያ ጣቢያ የጊዜያዊ ትምህርት ቤት አስተባባሪ መምህር ደሳለኝ ንጉሴ በበኩላቸው ከቀያቸው ተፈናቅለው ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩ ከ900 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጊዜያዊ ትምህርት ቤቱ ቅድመ መደበኛን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል  ያሉ ተማሪዎች ከሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


በወለህ መጠለያ ጣቢያ በጊዜያዊ ትምህርት ቤት ከሚማሩ መካከል ተማሪ ተሻለ ወልደሥላሴ  በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ መቆየቱን  ገልጿል።

ትምህርቱን ካቋረጠ አንድ ዓመት እንደሞላው ያስታወሰው ተማሪ ተሻለ "አሁን ላይ በተጠለልንበት የመጠለያ ጣቢያ የመማሪያ ክፍል ተዘጋጅቶ ትምህርቴን መጀመር በመቻሌ አስደስቶኛል" ብሏል።

በመጠለያ ጣቢያው ትምህርት መጀመሩ የተማሪዎች ከሥነ ልቡና ጉዳት በማውጣት ጊዜያቸውን በትምህርት ለማሳለፍ እንዳስቻላቸው ተናግሯል።


በአሸባሪው ህወሓት ወረራ በመፈናቀሉ የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን  ከአንድ ዓመት በላይ አቋርጦ መቆየቱን የገለፀው ደግሞ ተማሪ በሬ ፀሐይ ነው።

አሁን በመጠለያ ጣቢያው ትምህርቱን መቀጠሉን ገልጾ "በትምህርቴ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እተጋለሁ" ብሏል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ115 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም