ከስንዴ በተጨማሪ አኩሪ አተርና ሩዝ በስፋት በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዘይት እጥረትን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

76

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከስንዴ በተጨማሪ አኩሪ አተርና ሩዝ በስፋት በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዘይት ፋብሪካዎችን የግብዓት እጥረትን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ግርማሜ ጋሩማ ግብርና በውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማቅረብ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት የሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ ነው ይላሉ።

ዘርፉን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና ግብዓት በመደገፍ አገራዊ የምግብ ፍጆታ ማሟላት፣የውጭ ምርቶችን መጠን ማሳደግና ገቢ ምርቶችን መተካት ትኩረት እንደተደረገ ገልጸዋል።

በአሥር ዓመቱ የልማት እቅድ ላይ የምግብና ወጪ ንግድ ሰብሎችን ማሳደግ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡

በተለይ ከ60 ዓመታት በፊት ጀምሮ አገራዊ ፍላጎትን ለመሸፈን ከውጭ ሲገባ የቆየውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ኩታ-ገጠም እርሻን በመጠቀም የስንዴን ምርታማነት በሄክታር ከ30 ወደ 45 ኩንታል በላይ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፤ በመኸር ብቻ ሳይሆን በሁሉም ወቅቶች ስንዴን በማምረት አገራዊ ፍጆታውን መሸፈን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በዚህም በበልግ እና በመኸር 15 ሚሊየን ሄክታር በስንዴ እየለማ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት 400 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ ይህን ወደ 1 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ማድረግ ከተቻለ በአጠቃላይ በዓመት በመስኖ ብቻ 30 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት እንደሚቻል አብራርተዋል።

በዚህም ከውጭ የሚገባውን እስከ 25 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በአገር ውስጥ መተካት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ሌላኛው የግብርና አንኳር ጉዳይ የምግብ ዘይት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ የቅባት እህሎችን ብታመርትም 96 በመቶ የምግብ ዘይት ከውጭ ታስገባለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምታመርተው የቅባት እህል በአገር ውስጥ ያለውን 50 በመቶ የዘይት ፍላጎት ብቻ የመሸፈን አቅም እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም የቅባት እህሎች ምርት መጠን በማሳደግና በአገር ውስጥ በማቀነባበር የዘይት ፍላጎትን ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅባት እህሎች መካከል አኩሪ አተር ውጤታማ ሙከራዎች ማሳየቱን ገልጸው፤ በተያዘው ምርት ዘመን ምርቱን በማሳደግ የዘይት ምርት እጥረትን ለማሻሻል እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት 200 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ የሩዝ ምርትን ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባም ነው የገለጹት፡፡

በመሆኑም በሶማሌ  ክልል፣ በደቡብ ኦሞና ለሩዝ ምርት ምቹ በሆኑ ሌሎች አካባቢዎች  ሩዝ በስፋት ለማምረት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም