መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችና አገልግሎቶችን ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገቡ ሲደረግ የስግብግብ ግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል

242

ሚያዝያ 05 ቀን2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችና አገልግሎቶችን ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ (ፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ በኩል እንዲገቡ ሲደረግ የስግብግብ ግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ያለ ውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገቡ መደረጉ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2017/18 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው 10 አይነት እቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በፍራንኮ ቫሉታ የተፈቀዱ እቃዎችና አገልግሎቶች በጉምሩክ በኩል እንዲገቡ ሲደረግ የስግብግብ ግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፍራንኮ ቫሉታ ተጠቃሚዎች ለመንግስት የሚከፍሉትን ግብር ለመቀነስ በማሰብ የተጭበረበረ የሰነድ ማስረጃ ይዘው ሊመጡ የሚችልበት እድል ሊኖር ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በሰው ችግር ለመበልጸግና የራስን ጥቅም ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ የመንግስትን የመቆጣጠር ሃላፊነት አብዝቶበታል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መጥፎ ነገሮችን መቆጣጠር ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም ከመጥፎ ድርጉት በመቆጠብ ለውሳኔ ውጤታማነት መትጋት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን የእቃዎቹ አማካኝ የዋጋ መጠን በጉምሩክ ኮሚሽንና በባለሙያዎቹ የሚታወቅ ቢሆንም የህዝብና የአገር ጉዳይ የማያስጨንቃቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ በጋራ መቆጣጠር ይገባል ብለዋል፡፡

መድሃኒት፣ ነዳጅና ማዳበሪያን ጨምሮ በፍራንኮ ቫሉታ የገቡት አስሩ እቃዎች ከአጠቃላይ የገቢ ንግዱ 41 በመቶ ወይም 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የሚሸፍን ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና የውጭ አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለጠየቁት የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ምላሽ ለመስጠት መወሰኑን መግለጹ ይታወቃል፡፡

በፋይናንስ ዘርፍ ከ60 አመት በላይ በማገልግል የካበተ ልምድ ያላቸው የምጣኔ ሃብት ምሁሩ እየሱስወርቅ ዛፉ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ /ፍራንኮ ቫሉታ ማስገባት በሌሎች አገሮችም የተለመደ አሰራር መሆኑን ይናገራሉ።

መንግስት ለሀገር አስፈላጊ የሆኑ እቃዎችና አገልግሎቶችን ከውጭ ማምጣት የማይችል ከሆነና የግድ መግባት ካለባቸው ፍራንኮ ቫሉታ የሚፈቀድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፍራንኮ ቫሉታ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ እቃዎችና አገልግሎቶችን በመንግስት አቅም ብቻ መሸፈን ሳይቻል ሲቀር የሚደረግ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ ግጭትና ከአሸባሪው ህወሀት ጋር የነበረው ጦርነት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ያልተመጣጠነ የወጭና ገቢ ንግድ በመፍጠር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ፈትኖታል ብለዋል፡፡

ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝና ወተት የመሰሉ ምርቶች በጉምሩክ በኩል በቀጥታ እንዲገቡ ማድረጉ የእለት ጉርስን ከማሟላትም ባለፈ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል፡፡

ለአብነት የተቋቋሙት የዘይት ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንዲገቡ ካልተፈቀደ ዘይት ማምረት አይችሉም፤የኑሮ ውደነት እየተባባሰ ረሃብ እንዲከሰት ያደርጋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት አሁን አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ፍራንኮ ቫሉታ መፍቀዱ ትክክለኛና ወቅቱን የዋጀ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡