በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የጤና ስርአት ለመዘርጋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ካናዳ እገዛ ታደርጋለች

347

ሚያዚያ 4/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የጤና ስርአት ለመዘርጋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ካናዳ የበኩሏን እገዛ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን፤ የካናዳና ኢትዮጵያ የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር እንድታልፍ ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠው የኢትዮጵያን የተለያዩ የልማት ጥረቶችም ትደግፋለች ብለዋል።

በተለይም "ሴቶችን ማዕከል ያደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እየደገፍን እንገኛለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶችን ያማከለ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ በሰላምና ደኅንነት ጉዳይ እንዲሁም የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ካናዳ የበኩሏን እገዛ እያደረገች መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።  

በኢትዮጵያ ለሚካሄደው አገራዊ ምክክር ካናዳ በአዎንታዊ ጎኑ የምትቀበለውና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ታምናለች ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ሁሉን አቀፍና ግልጽ የፖለቲካ ሂደቶች ሊኖሩት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።  

በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጠያቂነትና የፍትህ ሥርዓት ገቢራዊ ማድረግም ወሳኝ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።    

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የወሰነችው የተኩስ አቁም ውሳኔ ተገቢ መሆኑን ገልጸውላቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የካናዳ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ትብብር መርኃ-ግብር አንዷ አገር መሆኗን ገልጸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2022 ኢትዮጵያ 43 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ እንደተቀበለች ተናግረዋል።

የገንዘብ ድጋፉም በኢትዮጵያ ጦርነቱን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚውል መሆኑን አስረድተዋል።

ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች መሳካት የሚያግዝ 74 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ድጋፍ ለማድረግና በኢትዮጵያ የሥርዓተ-ጾታና የሥነ-ተዋልዶ ጤና ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት እያገዘች መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የካናዳ መንግሥት ይፋ ባደረገው ስደተኞችን የማቋቋም መርኃ-ግብር በመታገዝ በኢትዮጵያ ስደተኞችና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያና የካናዳ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1965 ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም