ጀርመን ለኢትዮጵያ የግል ዘርፍ እድገት የ25 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

226

ሚያዚያ 5/2014/ኢዜአ/ ጀርመን ለኢትዮጵያ የግል ዘርፍ እድገት በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) በኩል የሚተገበር የ25 ሚሊየን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች።

የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያዘጋጁት የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሺሰማ ገብረሥላሴ እንደተናገሩት፤ መንግስት በተለይ የአምራች የኢንደስትሪ ዘርፉን እድገትና ተወዳዳሪነት ለማሻሻል እየሠራ ነው።

የጀማሪ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር ከአጋር አገራት ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤  በዚህ ረገድ ጀርመን ይፋ ያደረገችውን ፕሮጀክት ለአብነት አንስተዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በዘርፉ ያሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማጎልበት እንደሚያግዝም ነው ያነሱት፡፡

መንግስት ለፕሮጀክቱ እውን መሆን የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም ነው የተናገሩት፡፡

በ”ጂ አይ ዜድ” ኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እድገት ኃላፊ አረጋሽ አስፋው በበኩላቸው ፕሮጀክቱን ለመተግበር በተለያዩ ክልሎች ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባንኮች ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች እንጂ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በቂ የብድር አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።

በተጨማሪ ኢንተርፕራይዞቹ የአቅም ክፍተት እንዳልባቸውም በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰው፤  ከዚህ አኳያ ጂ አይ ዜድ ችግሩን ለመቅረፍ ድጋፍ ከሚያደርጉ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር ይሰራል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚተገበርም ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ባለሃብት ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አድማሱ ይፍሩ፤ ፕሮጀክቱ በአቅም ግንባታ እንዲሁም በአሰራርና አደረጃጀት ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያብራሩት፡፡

በተጨማሪም ዘርፉ በተሻለ የህግና ፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲመራ እገዛ እንደሚያደርግም እንዲሁ፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ፣ የጀርመን ኤምባሲ እና የጂ አይ ዜድ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለሃብቶች ተገኝተዋል።