የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት የተዘጋጁት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የዳያስፖራው ሁለገብ ጥረት ያስፈልጋል

223

አዲስ አበባ ሚያዝያ 5/2014 /ኢዜአ/ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለመጉዳት እንዲሁም ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት ለማስወጣት የተዘጋጁት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ዳያስፖራው ሁለገብ ጥረት እንዲያደርግ ተጠየቀ።

በቨርጂኒያ ግዛት የሚገኘው የ’ፑሽ ስታርት’ ሚዲያ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ቤቲ ተከስተ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራት ቆይታ እንዳለችው ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የምታገኛቸውን የልማትና የደህንነት ድጋፎች የሚያስቆሙ ናቸው።

በተለይም የልማት ድጋፎች መቆም በተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ በሆነው ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ትናገራለች።

አሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን በማስተባበር ለኢትዮጵያ እርዳታና ድጋፍ እንዳያደርጉ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑንም ገልፃለች።

በረቂቅ ህጉ ላይ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መሳሪያና የመሳሪያ መለዋወጫዎችን እንዳትገዛ ጭምር የሚከለክሉና ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት ውጪ የማድረግ አላማ ያላቸው መሆናቸውንም ጋዜጠኛዋ ተናግራለች።

ከሌሎች አገራት መሳሪያ ከገዛች ደግሞ አሜሪካ በሻጭ ሀገራት ላይ ማዕቀብ እንድትጥል ድንጋጌ  የሚያስቀምጥ ስለመሆኑ ጠቁማ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጭምር ጫና የሚያሳድር ነው ብላለች።

የረቂቅ ሕጎቹን ይዘት መንግስትን ከመደገፍና ከመቃወም ጋር የሚያያዝ ሳይሆን አጠቃላይ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ችግር የሚጋርጥና ሕዝብን የሚጎዳ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ነው ያለችው።

በመሆኑም ረቂቅ ሕጎቹ ከጸደቁ ኢትዮጵያን ከዓለም የፋይናንስ ስርዓት የሚያስወጡ እና በሉዓላዊነቷ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ሁሉም በጋራ ተቃውሞውን ሊያሰማ ይገባል ብላለች።

በተለይም የዳያስፖራው ማሕበረሰብ የኢትዮጵያን ትክክለኛ እውነታ ለዓለም በማስረዳትና ረቂቅ ሕጎቹን በፅኑ መቃወሙን አጠናክሮ መቀጠል አለበት በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ረቂቅ ሕጎቹ በአሜሪካ ምክር ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ባላቸው የ’ዴሞክራት’ና የ’ሪፐብሊካ’ን ፓርቲ አባላት ድጋፍ ማግኘታቸውን አንስታለች።

ከዚህም አልፎ ሕጎቹ በአግባቢ ድርጅቶች ግፊት ወደ ሕግ አውጪው ምክር ቤት እንዲደርሱ መድረጉን ጋዜጠኛ ቤቲ አስታውሳለች።

በተለይም ‘ኤች.አር 6600’ ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ድጋፍ በማግኘቱ በኮንግረሱ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ መታየት ቢኖርበትም እሱን አልፎ በቀጥታ ለኮንግረሱ መድረሱን አክላለች።

በአሁኑ ሰአት ሁለቱን ረቂቅ ሕጎች ኮንግረሱና ሴኔቱ እንዲያያቸው በኮሚቴዎች መመራታቸውንም ጠቅሳለች።

ይህም ቢሆን በዚህ ጊዜ ሕጎቹ በቀጥታ ድምጽ ሊሰጥባቸው እንደማይችልና ቀሪ የሕግ ሂደቶች እንዳሉ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብላለች።

በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ረቂቅ ሕጎቹ ድምፅ እንዳይሰጥባቸው ተሰሚነት ያላቸውን የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች የማሳመን ስራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁማለች።

በተለይ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲን በስልክ በማነጋገርና ደብዳቤ በመጻፍ በእጇ ላይ የሚገኘው የኤች.አር 6600 ለኮንግረስ በአጀንዳነት እንዳታቀርበው ጥረት እየተደረገ ነው ብላለች።

የአሜሪካ የሕግ አስፈጻሚው አካል ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ማሻሻል እንደሚፈልግ እየገለጸ ባለበት ወቅት ረቂቅ ሕጎቹ መውጣታቸው ግራ የሚያገባ መሆኑንም ጋዜጠኛ ቤቲ ተናግራለች።

በመሆኑም ዳያስፖራው ግራ ሳይጋባ በአንድነት ሕጎቹ ሊጸድቁ የሚችሉበትን እድሎች ለመዝጋት ሁለገብ ትግል እንዲያደርግ ጠይቃለች።

ኤች.አር 6600 ረቂቅ ሕግ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

የኤች.አር 6600 አጋዥ የሆነው ኤስ 3199 ረቂቅ ሕግ የአሜሪካ ሴኔት እ.አ.አ በ2022 ዓ.ም ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት መወሰኑ ይታወሳል።