ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሄደችበትን መንገድ በዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ላይ ታጋራለች

504

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 03/2014(ኢዜአ)ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሄደችበትን መንገድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የምታጋራ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በመጪው ሰኔ ወር ስዊድን ስቶክሆልም ለሚካሄደው አለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር፤ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት  መድረክ አካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዛሬው ውይይት ዓላማ  ሀገርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጉዳዩ ዙሪያ ምክረ ሃሳብ ማሰባሰብ ነው።

ኢትዮጵያ ለዚህ ምክክር ከተመረጡት 58 ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸው ከውይይቱ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦች በስቶክሆልሙ ዋና መድረክ ላይ የሚንጸባረቁ ይሆናል ብለዋል።

ብክለት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የብዝሀ ህይወት መመናመን አካባቢን ከሚጎዱ መንስኤዎች መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን አዘጋጅታ እየተገበረች መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን በመረዳትና ይህንም ቀድሞ ለመተንበይ ከሚመለከታቸው የዘርፍ  ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚሁ መሰረት ከዚህ ቀደም ተጀምረው የነበሩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነትን ለመገንባት የሚተገበሩ ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ መፍትሄዎች ተቋሙ በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ተግባራቶች መካከል መሆኑንም አክለዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት  በቢልየን የሚቆጠር ችግኝ በየዓመቱ የመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርም  በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችል ስራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ይህንኑ የኢትዮጵያን ጥረት የሚያሳይ ተሞክሮ በስቶክሆልሙ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ላይ ይቀርባል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ ታዳሽ በሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየሰራች ያለው ስራ መነሳት ያለበት ምክረ ሀሳብ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የአርብቶና አርሶ አደሩ የኑሮ ማዕከል ያደረገ የአካባቢ ጥበቃ ስራን ከምግብ ዋስትና ጋር አስተሳስሮ ማቅረብም እንደሚገባ አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመቀነስና አይበገሬነትን ለመገንባት እንዲሁም የአኗኗር ዘዴን ማሻሻል ሌላኛው አጀንዳ መሆን ያለበት ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ስቶክሆልም +50 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጠቃላይ ጉባኤ የተጠራና ከ ሰኔ 2 እስከ 3 ቀን 2022 እ.ኤ.አ ድረስ በስቶኮልም ስዊዲን የሚካሄድ አለም አቀፍ ስብሰባ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም