በአርሶ አደሩ እየለማ የሚገኘው የበጋ ስንዴ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ያስችላል - ኢንስቲትዩቱ

438

ጎባ፤ ሚያዚያ 3/2014 (ኢዜአ) በባሌ ዞን የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በአርሶ አደሩ እየለማ የሚገኘው የበጋ ስንዴ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የውኃ አማራጮችን በመጠቀም በዞኑ አጋርፋና ደሎ መና ወረዳዎች ስንዴ እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሳ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ  ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ  የሰብል ምርምርና የቴክኖሎጂ ብዜት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ብሩ እንደተናገሩት ፤ ኢንስቲትዩቱ የአርሶና አርብቶ አደሮችን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ እየሰራ ነው።

ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝሪያዎችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ማድረስን  ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለድርቅ ተጋላጭ ወረዳዎች  ማብዛት ሊያጋጥማቸው ከሚችል ተያያዥ ችግር እንደሚያወጣቸው ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በስሩ በሚገኙ 17 የምርምር ማዕከላት ባለፈው ዓመት ብቻ ድርቅና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ20 በላይ የሰብል ዝሪያዎችን በምርምር አውጥቶ ለተጠቃሚው ለማድረስ በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በደሎ መና እና አጋርፋ ወረዳዎች እየተባዙ የሚገኙ ዝሪያዎችን ጨምሮ በሌላውም የባሌ አካባቢ በበጋው ወቅት ከ18 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እየለማ ነው።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት፤ በተለይም በአጋርፋ ወረዳ የከርሰ ምድር ውኃን በራሳቸው ጥረት በማውጣት ስንዴን እያለሙ የሚገኙት አርሶ አደሮችን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት ይሰራል፡፡

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በተለይም በደጋና ወይና ደጋ የአግሮ ኢኮሎጂ ላይ ታጥሮ የነበረውን ምርምሩን ወደ ቆላማ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ደሎ መና ወረዳ አርብቶ አደሮች ዘንድ በ64 ሄክታር ማሳ ላይ እየተባዛ የሚገኘው የስንዴ ዝሪያ የዚሁ ጥረት አካልና መልካም ተሞክሮ የቀሰምንበት ነው ብለዋል።

ከደሎ መና ወረዳ አርብቶ አደሮች መካከል አቶ አልይ ከድር በሰጡት አስተያየት፤ እያባዙ የሚገኙት የስንዴ ምርጥ ዘር በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸውን ድርቅ ለመቋቋም ይረዳናል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የአካባቢያቸው ኮቲቻ አፈር ብዙ ውኃ ስለሚፈልግ በተደጋጋሚ የሚያለሙት ሰብል ከ20 ኩንታል የማይበልጥ ዝቅተኛ ምርት ሲያስገኝ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመደራጀት የከርሰ ምድር ውኃን በማበልፀግ ስንዴን በመስኖ እያለሙ የተሻለ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ 88 የሰብል ዝሪያዎችና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚው ማድረሱን ከምርምር ማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም