ኢዜአ ተደራሽነቱን በማስፋት ግንባር ቀደምትነቱ ጎልቶ እንዲወጣ መስራት እንዳለበት ተመለከተ

443

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 03/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት( ኢዜአ) ተደራሽነቱን በተደራጀ አግባብ በማስፋት ግንባር ቀደምትነቱ ጎልቶ እንዲወጣ መሰራት እንዳለበት ተመለከተ።

ኢዜአ የተመሰረተበትን 80ኛ  ዓመት ምክንያት በማድረግ  በባህር ዳር ከተማ የተዘጋጀና ለሶስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ የቆየው አውደ ርዕይ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

አውደ ርዕዩን ከጎበኙት መካከል የአማራ ክልል ሥራ አመራር አካዳሚ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጋሻው ገብሬ በሰጡት አስተያየት፤ ኢዜአ ለረጅም ዘመናት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ  ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ሲያገለግል የቆየ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

አውደ ርዕዩ ኢዜአ መረጃ ለማሰባሰብና ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ይገለገልባቸው የነበሩ መሳሪያዎችና አደረጃጀት እንዲሁም የአሁኑ ግዙፍ የሚድያ ተቋም መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሚዲያ  ረጅም ታሪክ ያለው ፣ የኢትዮጵያን የዘመናት የድልና የፈተና ጉዞ የተጋራ ግንባር ቀደም ሚዲያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የውጣ ውረድ ጉዞም ሆነ አሁን በቅርቡ በተከናወነው የህልውና ዘመቻ ሃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም  መሆኑን አንስተዋል።

መንግስታት ቢቀያየሩም የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እየዘገበ ለሌሎች ሚዲያዎች በማድረስ ሃላፊነቱን ሲወጣ የቆየና አሁንም የቀጠለ መሆኑን መረዳት እንደቻሉም አብራርተዋል።

ወደ ፊት ማህበረሰብ ተኮር አደረጃጀቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የበለጠ ተጠናክሮ መውጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ተደራሽነቱን በተደራጀ አግባብ በማስፋት በግንባር ቀደምትነቱ ጎልቶ እንዲወጣ መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።

አውደ ርዕዩ ኢዜአ በሀገሪቱ ያለውን የሚዲያ ችግር ተጋፍጦ የህዝብ አለኝታነቱንና ተቀባይነቱን ያሳየበት እንደሆነ መረዳታቸውን የተናገሩት ደግሞ ዶክተር ግርማ መለሠ ናቸው።

''ብዙ የሚዲያ ተቋማት ተመስርተው ብዙም ርቀት ሳይሄዱ ቀጭጨው ይቀራሉ'' ያሉት ዶክተር ግርማ ኢዜአ ግን ችግሮችን በመቋቋም ለ80 ዓመታት የዘለቀና ለሌሎችም አርአያ ሊሆን የሚችል ተቋም እንደሆነ ነው የገለጹት።

ቀጣይ የኢትዮጵያን እውነታ ለውጭው አለም በማስተዋወቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ለውጭው አለም ትክክለኛውንና ወቅታዊ መረጃን የማስተዋወቅ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰው፤ ኢዜአ ልምዱን ተጠቅሞና አቅሙን አዳብሮ የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም እየገጠሙ ያሉ ክፍተቶችን ሊሞላ ይገባል ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን  በበኩላቸው፤

አውደ ርዕዩ ኢዜአ የካበተ ልምድ ያለው የሚዲያ ተቋም እንደሆነ የተረዱበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢዜአ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር እራሱን በጽናት በመቆም ለሌሎችም ምሳሌ መሆን የሚችል አንጋፋ የዜና ምንጭ ነው ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ ሙሉዓለም ባህል ማዕከል በተካሄደው አውደ ርዕይ ላይ የኢዜአን የ80ኛ ዓመት ጉዞ የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ፣ የቪዲዮ ምስል እና  ይጠቀምበት የነበሩ መሳሪያዎች የቀረቡ ሲሆን የፌደራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመልክተውቷል።

ቀደም ሲልም በዋናው መስሪያ ቤትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት እንዲሁም በአዳማ ከተማ በተመሳሳይ ዝግጅቶች የአዜአ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መከበሩ በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም