በኦሮሚያ ክልል ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የልማትና የፀጥታ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

474

መጋቢት 12/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የልማትና የፀጥታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ የክልሉን የሶስተኛው ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም አመራሩ የልማት ስራዎችን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እያጣጣመ መምራት መቻሉንና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ በጥንካሬ መነሳታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኀብረተሰቡ በሁሉም መስክ የሚያደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም ነው ያነሱት፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን ኀብረተሰቡን በማሳተፍ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ተግባር በሁሉም አከባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከመተግበር አንጻር ግን ክፍተት መኖሩ ተገምግሟል ነው ያሉት፡፡

የመንግስት መዋቅር ውስጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ ከማጎልበት አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውም እንዲሁ፡፡

አሸባሪው ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍና የጸጥታ መዋቅሩን በማገዝ ጸጥታ የማስጠበቅ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የክረምት የእርሻ ልማት፣ የፕሮጀክት ስራዎችን ማፋጠን እና ግብር መሰብሰብ የክልሉ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ስራ ማሰናበት የደረሰ እርምጃ መውሰዱንም አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም የህዝብን ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ በማይመልሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ኃላፊው ያረጋገጡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም