እጅ ጥምዘዛ

370

እጅ ጥምዘዛ የአሜሪካ ምክር ቤት የተሳሳተ አካሄድ

  • የዲፕሎማሲና ፖለቲከኛ ተንታኞች ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግን የአሜሪካ ሸውራራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የወለደው፣ የኤምፔሪያሊዝም ቅሪተ አስተሳሰብ መገለጫ ነው ይሉታል።
  • በምፀታዊ መልኩ “የኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዲሞክራሲ አክት/The “Ethiopia Stabilization, Peace, and Democracy Act” የተሰኘው የዚህ ሰነድ ይዘት በማር እንደተለወሰ መርዝ ነው።

የምዕራብ ዘመም ቅኝ ግዛት እሳቤ ዛሬ ድረስ አላቋረጠም። መልክና ቅርጹን እየለዋወጠ ሶስተኛ ዓለም በሚሰኙ አገራት ላይ ይሽከረከራል። ለዚህ ቅርብ ማሳያ ደግሞ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያረቀቁት “ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 የተሰኘው ረቂቅ ሕግ ነው። የዲፕሎማሲና ፖለቲከኛ ተንታኞች ረቂቅ ሕጉን የአሜሪካ ሸውራራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የወለደው፣ የኤምፔሪያሊዝም ቅሪተ አስተሳሰብ መገለጫ ነው ይሉታል። በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብቼ ካልፈተፈትኩ ከሚል እብሪት የተጠነሰሰ ሰነድ።

በአሜሪካ ሌይደን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል ተመራማሪና የአፍሪካ ፖለቲካና መልካም አስተዳደር ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ ትንታኔ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተቀረው ዓለም የሚካሄዱ አያሌ አንኳር ጉዳዮች ጆሮ እንዲነፈጋቸው አድርጓል ይለናል። ለማሳያነትም ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ለጂኦ-ስትራቴጂክ ጥቅሟ ኢትዮጵያን በፈለገችው ምሕዋር ለማሾር የምታደርገውን እረፍት የለሽ ጫና ያወሳል። አሸባሪው የሕወሃት ወራሪ ኅይል በአገሪቷ መከላከያ ኋይል ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ካደረሰበት ክስተት ጀምሮ ኢትዮጵያ ለመልከ ብዙ ምስቅልቅሎች ተዳርጋለች። አሜሪካ ይህ ቡድን ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ ካደረሰው ጥፋት ጉዞ ይልቅ ለግጭቱ የኢትዮጵያን መንግስትን መኮነኗን ቀጥላለች።

የፖለቲካ ተንታኞች ላለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ ገደማ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የተከተለችውን አቋም ከፖለቲካዊ አንድምታው ሲፈቱት ጉዳዩን በማዕቀብ ማስፈራራትን የመረጠ ግልጽ ጣልቃ ገብነት ያደርጉታል። የአገሪቷ ፖሊሲ የጦርነቱን መንስዔ በቀና ልብ ያልተመለከተ፣ ለግጭቱ መቋጫ መፍትሔ ለማበጀት የማይሻ አካሄድ ይሉታል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌላው ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ቀኝ እጇ የሆነው ዩኤስ አይዲ/USAID የኢትዮጵያን መንግስት የሰላም ጥረት በገሀድ የካዱና አመክንዮ ቢስ አቋም የመረጡ እንደሆኑ አጋልጠዋል።

የጦርነቱን ቀስቃሽ የህወሃት ቡድን የሚያወግዝ ደፋር ልብ ያጣ፣ የአሸባሪውን ቡድን ቀለብተኞች ጩኽት የሚያስተጋባና መንግስት ላይ ተጨማሪ ጫና ያበረታ አቋም ነበራቸው። ይህ አካሄድ ዛሬም አልተቀየረም። የአሜሪካ ምክር ቤት ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማጠንጠኛ ማዕከል የተለየ ባለመሆኑ ኤች አር 6600 ረቂቅ ህግን በማቅረብ ኢትዮጵያን በማዕቀብ ማስፈራሪያ እጇን ለመጠምዘዝ አቋሙን አጠናክሯል። ምክረ ሃሳቡ በምፀታዊ መልኩ “የኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላምና ዲሞክራሲ አክት/The “Ethiopia Stabilization, Peace, and Democracy Act” የተሰኘው ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ ያለውን ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለመደገፍ የሚል ነው።

የበይነ መረብ ጥላቻ ንግግርን መዋጋት፣ በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ በደል የፈጸሙ ሃይሎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት መደገፍ፣ ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ማገዝና መሰል ርዐሰ ጉዳዮችን ማቀፉ በእርግጥም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጎ ሃሳብ ያዘለ ይመስላል። ሐቁ ግን በማር የተለወሰ ሬት ነው። ግጭቱ በሰላም እንዳይቋጭ ሴራ ለሚጎነጉኑ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ በሙስና የተዘፈቁና ለፅንፈኛ ቡድኖች የጦር መሳሪያ በሚያስታጥቁ ግለሰቦች ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ማዕቀብ እንዲጥልባቸው በምክረ ሃሳቡ ተቀምጧል።

በሌላ መልኩ መንግስት ጥቃት ከመፈጸም እስኪታቀብ፣ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲሳካ እገዛ ማድረጉ እስኪረጋገጥ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻል እስኪያሳይ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን እስኪፈቅድና የጦር ወንጀል የፈጸሙ አካላት ላይ ምርመራ እስኪያደርግ ድረስ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚደረገው የጸጥታና የደህንነት ማስጠበቂያ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል፡፡ በዓለም ባንክ፣ የአለም የገንዘብ ድርጅትና መሰል ዓለም አቀፍ የፋይናስ ተቋማት ምንም አይነት ድጋፍና ብድር ለኢትዮጵያ እንዳይሰጡ ይከለክላል፡፡ ምክረ ሀሳቡ ሲደመድም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ የጦር ወንጀል፣ የመብት ጥሰት እና የዘር ማጥፋት ክስ እንዲመሰረትም ያሳስባል፡፡ በጥቅሉ ምክረ ሀሳቡ በከንቱ መላምቶችና ግራ አጋቢ መነሻዎችን መሰረት በማድረግ አሜሪካ ያለምንም ከልካይ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ የሚጎተጉት ነው።

ኤች.አር 6600 በይዘት ደረጃ ሲተነተን ያነሳቸው ጥያቄዎች ቀድሞውኑ በኢትዮጵያ የተመለሱ እንደሆኑ ማየት ይቻላል። የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት እንዲኖርና አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ቢጠይቅም ሳታማኽኝ ብላኝ’ ይሉት ብሂል ካልሆነ በስተቀረ የተጠቀሱ እንኳር ጉዳዮች ላይ መንግስት ምንም ችግር እንደሌለበት የገለጸበትና ከውስን ሀብቱ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ በተግባር የመለሳቸው ናቸው።

የሰነዱ ጥቅል ሃሳብ አንድም ጊዜ የአሸባሪውን ቡድን የጦር ወንጀል አለመጥቀሱ የህወሃት ጋሻ ጃግሬዎች የምክረ ሃሳቡ ተባባሪ አዘጋጅ በመሆናቸው ላያስደንቅ ይችላል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ማዕቀብ በጦርነቱ ጠንሳሾችና ጦር ወንጀለኞችን አልፏቸዋል። በአፋርና አማራ በደረሰው ልብ ሰባሪ ሰብዓዊ ውድመት ዘንግቶ አንድን ቦታ ብቻ ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ቀውስ የተዳረገ ማስመሰሉ የማንም ንጹህ ህሊና አይቀበለውም።

ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በአማራና አፋር ክልሎች ከፍተኛ የምግብ፣ መድኃኒትና ነዳጅ አቅርቦት ችግር መኖሩና በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ በሁሉም ወገን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙም አይካድም። የኢትዮጵያ መንግስት ጥፋቱን በፈጸሙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በፍርድ ቤት የታገዘ ህጋዊ እርምጃ የወሰደ ሲሆን በህወሃት ወራሪ ቡድን አባላት ለፈጸሙት ግፍና በደል ግን እስካሁን የተወሰነ ውሳኔ ስለመኖሩ አልተሰማም።

የአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ሐምሌ 2013 በኢትዮጵያ መንግስት የታወጀውን የተኩስ አቁም በመናቅ በአፋርና አማራ ክልሎችን በመውረር በበቀልና እብሪት እሳቤ መጠነ ሰፊ ጥፋት አድርሷል። ይህ የቡድኑን የግጭቱ ጠንሳሽ፣ ቀስቃሽና አነሳሽ መሆኑን ያሳያል።

የመንግስት ሰራዊት ከሀምሌ 2013 ጀምሮ ከትግራይ ለቆ ከወጣ በኋላ በክልሉ ምንም አይነት ጦርነት ባይካሄድም አማራና አፋር ክልሎች ግን የደም መሬት ሆነዋል፡፡ ወራሪው ኃይል አሁንም በሃይል የያዛቸው ስፍራዎች አሉ። ወራሪው ኃይል ያደረሰው ውድመት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና አሰቃቂ ግፎች አለምአቀፍ ህግጋትን የጣሰ፣ በከፍተኛ የጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆንም ቅሉ ምዕራባዊያን የአጉራሽ ነካሽ ላለመሆን ዝምታን መርጠዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ ወረራ ከሁለቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎች ሀብትና ንብረታቸው ወድሞ የመንግስትንና የረጂ ድርጅቶችን እጅ እርጥባን ጠባቂ ሆነዋል።  በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ደግሞ የህወሃት ዕኩይ ዓላማ ባነገበው የሸኔ ቡድን በተደጋጋሚ የብሔር ተኮር የጥቃት ሰለባ ሆነው ቀጥለዋል። ከጥቃቱ ያመለጡ ዜጎችም ወደ አማራ ክልል ተፈናቅለው ይንገላታሉ። የኤችአር 6600 ረቂቅ ሰነድ ግን የእነዚህ ዜጎች ጉዳይ አይገደውም። በሱዳንና ግብጽ የሚደገፉ የጉምዝ አማፂ ቡድን በንጹሃን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አያወግዝም።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሳምንት በፊት ሰብዓዊ ድጋፎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ቢፈቅድም በፕሮፓጋንዳው ዓለም ደጋፊዎቹን ያበዛው የህወሃት ቡድን ግን የቀረበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አማራጭ ወደ ኋላ በመግፋት ጦርነት ቅስቀሳውን ቀጥሎበታል፡፡ በዕለቱ የመንግስትን የሰላም ሀሳብ እንደሚቀበል ቢገልጽም በአፋር ላይ የጀመረውን ጦርነት አላቆመም። ሽብር ግብሩ ለሆነው ቡድን ሰላምና መረጋጋት በፍጹም አልተዋጠለትም። በጥላቻ ተወልዶ በጦርነት ወደ መቃብር አፋፍ የተጠጋው ቡድን ገና አልተቀበርኩም በማለት በጣዕረ ሞት እየተወራጨ ነው፡፡

የኤች አር 6600 ምክረ ሃሳብ በህዝብ ድምጽ በተመረጠ መንግስት ላይ የወረደና በሕግና በሞራል ተቀባይነት የሌለው ዱብ እዳ ብቻ ሳይሆን የሁለቱን አገራት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በእጅጉ የሚያሻከር ነው፡፡

በምክረ ሃሳቡ የተነሳው ማዕቀብ የኢትዮጵያን መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ክፉኛ ይጎዳል። በተለይም በአሜሪካ አገር ግማሽ ምዕተ አመት ኖረው፣ ወልደው ከብደው ለሚኖሩ በአሜሪካ ሲመኩ የኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ልብ ሰባሪ መርዶ ነው። በአገረ አሜሪካ በሚኖሩ ዘመዶቻቸው ድጋፍ ህይወታቸውን ለሚመሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ እና በንግድ ትስስር  የኢኮኖሚ ወዳጅነት ለመሰረቱትም አይበጅም።

የሀገራቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ረቂቅ ሰነዱ ይህንን ሁሉ አብሮነት ገደል የሚከት በመሆኑ ሁሉም ሊታገለው ይገባል፡፡ በአብሮነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውንና የሁለቱን አገራት የዘመናት ግንኙነት ያጠለሻል። አርቀው ማስተዋል፣ ማሰብ በተሳናቸው ጠባብ አዕምሮ ባላቸው ሰዎች የቀረበ እና ሁኔታውን ወደ ባሰ መቀመቅ የሚያወርድ ነው።

የአሜሪካ መንግስት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት አስወጥቷል። ይህ እርምጃ ከመንግስት ይልቅ ድሃውን ማህበረሰብ በተለይ ሴቶችን በእጅጉ ጎድቷል። ኤች አር 6600 የተሰኘው ምክረ ሃሳብ የኢምፔሪያሊስት እሳቤ የታጨቀበት፣ ኢትዮጵያን በፈጠራ አሉባልታና ክስ በመታገዝ ለመቆጣጠር የሚደረግ ሙከራ አካል ነው።

የባይደን አስተዳድር ለ10 አመት ተብሎ በተረቀቀው ኤች አር 6600 ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በማህበራዊ ሚዲያ የፈጠራ ወሬ፣ በጉዞ ክልከላ፣ በውስጥ ፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ አሻጥር፣ አለም አቀፍ ብድርና ድጋፍ ክልከላ ዕጅ ለመጠምዘዝ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ የመልማት ጥያቄ በማንም ይሁንታ የሚሰራ ወይም የሚከለከል አይደለም። በምክረ ሃሳቡ ላይ በአንቀጽ 6(c) ላይ ግን ኢትዮጵያ ድጋፍ ማግኘት የምትችለው ለመሰረታዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶች “ብቻ ነው ይላል፡፡ ይህ በኢኮኖሚ እጅን የመጠምዘዝ አካሄድ ኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ፊቷን እንድታዞር እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም፡፡  ምክረ ሃሳቡ ከጸደቀ የኢትዮጵያን የልማትና ዕድገት ጉዞ ያሰናክላል፤ ከፍተኛ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ወድመት ያስለትላል።

የአሜሪካ መንግስት ምክር ቤት ከልቡ በኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት እንዲሰፍን የሚፈልግ ከሆነ ሚዛናዊ የሆነ አካሄድን መከተል ነበረበት። ለጉዳዩ ጠለቅ ያለ ትንታኔ በመስራት መፍትሄ ማበጀት ያሻል።

ከሁሉም በላይ ጥቃቱን የጀመረው፣ ክልሎችን ወሮ ያወደመው፣ የፌደራል መንግስቱን በኃይል ለመገልበጥ የሞከረው፣ ኢትዮጵያን ወደ አለመረጋጋት የከተተው፣ የጅምላ ግድያና  ቁሳዊ ውድመት ያደረሰው፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር የሚዘውረው አካል ማን ይሆን የሚለውን በገለልተኛ ቡድን አስጠንቶ ውሳኔ መስጠት ይገባል። የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየተንቀሳቀሰ ነው። የአሜሪካ መንግስትም በህወሃት ላይ ጫና አሳድሮ ከወረራ እንዲታቀቡ ማድረግ እና በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም