በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ የሰላምና የልማት ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ አለብን - የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ የሰላምና የልማት ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ አለብን - የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ፣ ሚያዝያ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ በክልሉ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በአዳማ ገልማ አባ ገዳ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ የመንግስት የሶስተኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ሶስት ወራት በአሰራርና በዕቅድ ከመምራት አንፃር ተስፋ ሰጪ ሂደቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የሰላም እጦት መንስኤዎችን ከመለየት፣ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ከማጥራትና መፍትሔ ከማበጀት አኳያ መልካም ጅምሮች አሉ ብለዋል ።
ህብረተሰቡ ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በባለቤትነት እንዲሳተፍ በማድረግ፣ በዜግነት አገልግሎት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የተሻለ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ የዕርከን ስራና ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ መካሄዱን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።
የልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ ሂደቶች የተለዩበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ለብልፅግና ጉዞ ስኬት መሰረት መጣል መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይ ሶስት ወራት በትኩረት የሚሰሩ ጉዳዮች መለየታቸውን ጠቁመዋል።
በተገኙ ስኬቶች ሳንዘናጋ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን መረባረብ አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።
በተለይ የበልግ አዝመራ፣ የመኸር እርሻ ማሳና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የኬሚካል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
የ2015 በጀት ዓመት የክልሉ የልማት ዕቅድ ዝግጅት፣ አማራጭ የገቢ ምንጮችን ማስፋትና ገቢን አሟጦ መሰብሰብ፣ የጤና አገልግሎት ማሻሻልና የትምህርት ሴክተር ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው።
የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ የመሬት አስተዳደር፣ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ማስወገድ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአፈፃፀም ላይ ያጋጠሙን ችግሮችን ለመፍታት ከወረዳ እስከ ክልል ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት የአፈፃፀም ውስንነትና ክፍተት የታየባቸው የልማት ፕሮጄክቶች የግንባታ መዘግየት፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንና ሸኔን ከማጥፋት አንፃር በቀጣይ ሰፊ ርብርብ የሚደረግባቸው አጀንዳችን ናቸው ብለዋል አቶ ሽመልስ።
"ግምገማው ችግሮቻችንን አንጥረን ያወጣንበት ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ያለው አመራር ህብረተሰቡን በማሳተፍ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በየደረጃው የሚቀርቡ ሪፖርቶች ተጨባጭ መሆናቸውን በማረጋገጥ ህብረተሰቡ የሚያነሳውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብን ያሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።
ሌብነትና የህዝቡን ህገ መንግስታዊ የሆነው አገልግሎት የማግኘት መብት በገንዘብ እንዲገዛ በሚያደርጉ አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህም በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፤ "ችግሮቹን በየደረጃው አጥርተን ወደ መስመር እናስገባለን" ነው ያሉት።
ለዚህም ተጠያቂነትን የሚያስከትል የአሰራር ስርዓት የማጠናከር ተግባር በትኩረት የምንሰራባቸው ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ